ሴካፋ ከ20 ዓመት በታች| ኤርትራ በሰፊ ውጤት ስታሸንፍ ተጨማሪ የሩብ ፍፃሜ አላፊዎችም ታውቀዋል

*ኢትዮጵያ ነገ የመጨረሻ ዕድሏን ትሞክራለች

የሴካፋ ከ20 ዓመት ዋንጫ ዛሬም በአምስተኛ ቀን ጨዋታ ሲቀጥል ሦስት ጨዋታዎች ተካሂደው ኤርትራና ደቡብ ሱዳን ድል ሲያደርጉ ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፉ ተጨማሪ ሀገራት ታውቀዋል።

በኤርትራ ዋናው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዓለምሰገድ ኤፍሬም እየተመሩ ላለፉት ስምንት ወራት ዝግጅት ያደረጉት የቀይ ባሕር ግመሎች ጅቡቲን 7-0 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የኤርትራን የድል ጎሎች ሮቤል ተክሌ፣ ዓሊ ሱሌማን፣ መዋዕል ተስፋይ፣ ስምዖን አስመላሽ፣ ሚካኤል ሀብቴ እና ኢማዒል ሱልጣን አስቆጥረዋል።

በዚሁ ምድብ የምትገኘው የውድድሩ አዘጋጅ ዩጋንዳ ከሱዳን ጋር ሁለት ለሁለት አቻ ተለያይታለች። ዩጋንዳ በስቴቭን ሴሬንኩማ እና ብራይት አኑንካኒ ጎሎች 2-0 መምራች ብትችልም አማር ካኖ እና ሙሐመድ ናሚር ሱዳንን ነጥብ ተጋርታ እንድትወጣ አስችለዋል።

ከምድቡ ያለፉ ሀገራት፡ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ

ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን ያገናኘው የምድብ ሐ ጨዋታ በደቡብ ሱዳን 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ዳንኤል ሶሎንግ፣ ጆሴፍ ስቴፈን እና ዎል ማክዌት ደቡብ ሱዳን በአራት ነጥቦች ቡሩንዲን በግብ ልዩነት በልጣ በአንደኝነት ወደ ሩብ ፍፃሜ እንድትገባ ያስቻሉ ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ከምድቡ ያለፉ ሀገራት፡ ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ

ውድድሩ ነገም ሲቀጥል ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ዛንዚበር ከ ታንዛንያ ይጫወታሉ። ጭላንጭል ተስፋ ይዛ ወደ ሜዳ የምትገባው ኢትዮጵያ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ የግድ ኬንያን ከማሸነፍ በተጨማሪ ዛንዚባር በታንዛኒያ ሽንፈት ማስተናገድ ይኖርባታል።

ከምድቡ ያለፉ ሀገራት – ኬንያ እና ታንዛኒያ

ማስተካከያ፡ በትላንትናው ዕለት “ኢትዮጵያ ከምድብ መሰናበቷን አረጋግጣለች” የሚለው ዘገባችን ስህተት በመሆኑ ” ኢትዮጵያ ከምድብ ለመሰናበት ተቃርባለች” በሚል እንዲታረም ከይቅርታ ጋር እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ