መቐለ 70 እንደርታዎች ሁለት ተጫዋቾች ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል

ያለፈው ዓመት የፕሪምየር ሊግ አሸናፊዎቹ መቐለዎች ባለፈው ዓመት ከሶሎዳ ዓድዋ ጋር አስደናቂ ዓመት ያሳለፈው ተስፈኛው አጥቂ ክብሮም አፅብሃ እና በ2010 የውድድር ዓመት በመቐለ 70 እንደርታ ሁለተኛ ቡድን ቆይታ የነበረው አብይ ተወልደ አስፈርመዋል።

ባለፈው ዓመት በሶሎዳ ዓድዋ ቆይታው አስራ ሶስት ግቦች በማስቆጠር ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ ያስቻለው ክብሮም አፅብሃ የባለፈው ዓመት የብሄራዊ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ከሌሎች ሁለት ተጫዋቾች ማሸነፉ ይታወሳል።ከዚ በፊት በአክሱም ከተማ እና ደሴ ከተማ መጫወት የቻለው አጥቂው በተሰጠው የሙከራ ግዜ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌን ካሳመነ በኃላ ነው ለክለቡ መፈረም የቻለው።

ሁለተኛው ለቡድኑ የፈረመው የቡድኑ የሁለተኛ ቡድን ተጫዋች አብይ ተወልደ ነው። ከሳምንታት በፊት በተጠናቀቀው የባሎኒ ፉትሳል ውድድር ላይ በሰላሳ ሰባት ግቦች የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ይህ ተጫዋች ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ አሳዳጊ ቡድኑ ይመለሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ