ቅዱስ ጊዮርጊስ የትምህርት መርጃ መሳርያዎችን ድጋፍ አደረገ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኀበር ከደጋፊዎች ጋር በጋራ በመሆን ለአራተኛ ጊዜ መማር እየቻሉ ሆኖም የትምህርት መርጃ መሳርያዎች እጥረት ላጋጠማቸው ተማሪዎች በ20 በጎ አድራጎት ማህበር ተቋማት በኩል በሸራተን ሆቴል ድጋፍ አደረገ።

በዝግጅቱ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ረ ፅዮን ተክሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኀበር ፕሬዝደንት አቶ አብነት ገ/መስቀል እና መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ወደ 20 የሚጠጉ የበጎ አድራጎት ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል። ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ በጎ ተግባር ክለቡ እና ደጋፊዎች በጋራ በመተባበር 700ሺ ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የትምህርት መሳርያዎች ድጋፍ ተደርጓል። የዘንድሮውን ድጋፍ ለየት የሚያደርገው ለኢትዮጵያ ዐይነ ስውራን ማኀበር የብሬል ወረቀት ስሌትና ኬን መበርከቱ እንደሆነ ከመድረኩ ሰምተናል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር ከ1968 ጀምሮ በተለያዩ በጎ ስራዎች ላይ እየተሳተፈ የቆየ ፋና ወጊ ክለብ መሆኑን በዝርዝር የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ይህ በጎ ተግባር ክለቡ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል። በዕለቱም ክቡር አቶ አብነት ገ/መስቀል ደብተሮቹን ለተቋማቱ ሀላፊዎች ካስረከቡ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ህዝባዊ ተቋም እንደመሆኑ ከእግርኳሱ ባሻገር በልዩ ልዩ ማህበራዊ መስኮች ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል። ወደፊትም አቅም በፈቀደ መጠን ደጋፊዎችን አስተባብሮ እገዛ ማድረጉን እንደሚቀጥል በመጠቆም አቶ አብነት በግላቸው ለ20 በጎ አድራጎት ተቋማት ማኀበር በዘንድሮ ዓመት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በመያዝ ለሚያጠናቅቁ ተማሪዎች በየዓመቱ የ5000 ብር ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

በዕለቱ ድጋፍ የተደረገላቸው የተቋማቱ ኃላፊዎች ይህ አንጋፋ ክለብ ላደረገላቸው ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም ክለቡ ይህንን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልክታቸውን በማስተላለፍ የምስጋና ሽልማት አበርክተዋል።

በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ፅዮን ተክሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ እጅግ የሚያስመሰግነው ተግባር ሲሆን በተለይ በየዓመቱ ለተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሳርያዎች ድጋፍ ሲደረግ ብዙ ጊዜ ለተዘነጉት ግን ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው ማየት የተሳናቸውን ድጋፍ መደረጉ ፋና ወጊ ተግባር ከመሆኑ ባሻገር ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ትልቅ ተግባር ነው በማለት ክለቡ እያደረገ የሚገኘውን በጎ ሀሳብ አድንቀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ