ሩዋንዳ ከመልሱ ጨዋታ በፊት የወዳጅነት ጨዋታ ታደርጋለች

በቻን ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያን የምትገጥመው ሩዋንዳ በቀጣዩ ሰኞ ታንዛኒያን በወዳጅነት ጨዋታ በሜዳዋ ታስተናግዳለች፡፡

በአሰልጣኝ ማሻሚ ቪንሰንት የሚመሩት ሩዋንዳዎች ከቀናት በፊት በመቀለ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ኢትዮጵያን 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ 2020 የቻን አፍሪካ ዋንጫ የተሻለ የማለፍ እድልን ይዘው ለመልስ ጨዋታ የተሻለ እድልን ሰንቀው መመለሳቸው ይታወሳል። በቀጣይ ላለባቸው የመልስ ጨዋታ እንዲሁም በቅርቡ ለሚጀመረው የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድም ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ታንዛኒያን በቀጣዩ ሰኞ በኪጋሊ ስታዲየም የሚገጥሙ ይሆናል፡፡

ሩዋንዳዎች ከኢትዮጵያ ጋር ካደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በፊት በወዳጅነት ጨዋታ ዲሪ. ኮንጎን 3-2 ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

ሩዋንዳ ኢትዮጵያን አሸንፋ ለ6ኛው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ከበቃች በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ የምትሳተፍ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ