አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማማ

ቀደም ብለው ሚካኤል ጆርጅን ያስፈረሙት አዳማ ከተማዎች ግብ ጠባቂው ደረጀ ዓለሙ እና ኃይሌ እሸቱን የግላቸው ለማድረግ ተስማምተዋል።

ያለፈውን የውድድር ዓመት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ጀምሮ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው ኃይሌ እሸቱ ከዚህ ቀደም ለአዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫውቷል። በድቻ እና ኤሌክትሪክ አብሯቸው ከሰራው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ሲሆን ለቋሚ ተሰላፊነትም ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።

ሌላው ክለቡን ለመቀላቀል የተስማማው ግብ ጠባቂው ደረጄ ዓለሙ ነው። ከዚ ቀደም በሰበታ ከተማ፣ ዳሽን ቢራ፣ ወልዲያ እና አዲስ አበባ ከተማ የተጫወተው ደረጄ ያለፈውን የውድድር ዓመት ከአሁኑ የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር በወላይታ ድቻ ያጠናቀቀ ሲሆን በአዲሱ ክለቡ ወደ ጊኒው ሆሮያ ያቀናው ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንካራን የሚተካ ይሆናል።

ሁለቱ ተጫዋቾቹ ከቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመሩ ሲሆን የዝውውር ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀም በቅርቡ ለክለቡ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ