በታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸው የነበሩ አምስት የዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተጫዋቾች ወደ እግርኳስ ተመለሱ

ከወራት በፊት ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸው ጉዳት አስተናግደው የነበሩ አምስት የዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተጫዋቾች ዳግም ወደ እግር ኳስ ተመልሰዋል።

ዋልታ ፖሊስ ትግራይ በሚያዚያ ወር አጋማሽ በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ጨዋታ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃንን ገጥሞ ወደ ከተማው በሚመለስበት ወቅት በአፋር አከባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ከባድ ጥቃት ሲደርስበት ጉዳት ያስተናገዱት ቢላል አባድር፣ ቢንያም ዘርዑ፣ ዳዊት ገብሩ እና ሓበን ዳንኤል ከጉዳታቸው ሙሉ ለሙሉ አገግመው ወደ ሜዳ ሲመለሱ በወቅቱ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ደረቱ አከባቢ የመተንፈሻ አካል ቀዶ ጥገና ያደረገው አማካዩ ኤፍሬም ኪሮስ በግሉ ቀላል ልምምድ እያደረገ ይገኛል።

በወቅቱ አነጋጋሪ በነበረው ጥቃት አማኑኤል ብርሃኑ የተባለ ተጫዋች ህይወቱ ሲያልፍ ከላይ የተጠቀሱት አምስት ተጫዋቾችን ጨምሮ በቡድኑ አባላት ቀላል እና ከባድ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና በትግራይ ከሚገኙት አንጋፋ ክለቦች ስሙ በግንባር ቀደምነት የሚነሳው ይህ ክለብ በትግራይ ፖሊስ ሥር የሚተዳደር ሲሆን በዚህ የውድድር ዓመትም በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሲሳይ (ኮማንደር) እየተመራ በአንደኛ ሊግ ይወዳደራል።


© ሶከር ኢትዮጵያ