አአ ከተማ ዋንጫ | ሳልሀዲን ሰዒድ የጊዮርጊስን ከምድብ የማለፍ ተስፋ አለመለመ

በምድብ አንድ ሌላኛው የዛሬ ጨዋታ በመጀመሪያ ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተቀይሮ በገባው ሳልሀዲን ሰዒድ ሁለት ግቦች ታግዘው ወልቂጤን 3ለ1 በማሸነፍ ከምድብ የማለፍ ዕድሉን አለምልሟል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ለቀድሞው የክለባቸው ታሪካዊ ተጫዋች አዳማ ግርማ የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡

በመጀመሪያው ጨዋታ በምክትል አሰልጣኝነት የተመለከትነው አዳነ ግርማ በዛሬው ጨዋታ በወልቂጤዎች በኩል በመጀመሪያ ተሰላፊነት ጨዋታውን መጀመር ችሏል፡፡

ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ማጥቃትን የመጀመሪያ ምርጫቸው አድርገው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

በግብ ማግባቱ ረገድ ቅድሚያውን የወሰዱት ወልቂጤዎች ሲሆኑ ሰልሀዲን በርጌቾ አደገኛ ቦታ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘው የቅጣት ምት አዳነ ግርማ በግሩም ሁኔታ በመምታት አስቆጥሯል ፤ ከግቡ መቆጠር በኃላም አዳነ ግርማ ለቀድሞ ክለቡ ደጋፊዎች ክቡሩን የገለፀበትን የደስታ አገላለፅ አሳይቷል፡፡

ከግቧ መቆጠር በሰከንዶች ልዩነት ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት በመጀመሪያ ንኪኪ ግብ ያስቆጠረው ዛቦ ቴጉይ የአቻነቷን ግብ በግንባሩ በመግጨት ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት አንድ አቻ እንዲለያዩ አስችሏል፡፡

ክፍት በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ ጊዮርጊሶች በደቂቃዎች ልዩነት መሪ ሊሆኑባቸው የሚችሉትን አጋጣሚዎች በዛቦ ቴጉይና በሳልሀዲን በርጌቾ አማካኝነት ቢያገኙም ሶሆሆ ሜንሳ በሁለቱም አጋጣሚዎች በአስደናቂ ሁኔታ ሊያድንባቸው ችሏል፡፡ በአንጻሩ ወልቂጤዎች በ62ኛውና በ66ኛው ደቂቃ ግሩም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ጌታነህ ከበደን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሳልሀዲን ሰዒድ በ71ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ግሩም ኳስ አክርሮ በመምታት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃ በኃላ በግሩም አጨራረስ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ቡድኑን ታድጓል፡፡

ወልቂጤ ከተማዎች ምንም እንኳን በሁለቱም የምድብ ጨዋታዎች ተሸንፈው ከወዲሁ መሰናበታቸውን ቢያረጋግጡም በሜዳ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን በሁለቱም ጨዋታ ላይ አሳይተዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ተቀይሮ በመግባት ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ሳልሀዲን ሰዒድ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ