ትግራይ ዋንጫ | ሲዳማ ቡና ወደ ፍፃሜ አልፏል

የትግራይ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ ሲዳማ ቡና ስሑል ሽረን አራት ለአንድ በማሸነፍ ወደ ፍፃሜው ማለፉን አረጋግጧል።

ጥሩ ፉክክር እና በርካታ የግብ ሙከራዎች በታዩበት ጨዋታ ገና በአራተኛው ደቂቃ ነበር ግብ ያስተናገደው ሃብታሙ ገዛኸኝ የተከላካዮች የቦታ አያያዝ ችግር ተጠቅሞ አምልጦ ግብ በማስቆጠር ቡድኑም መሪ ማድረግ ችሏል። በስድስተኛው ደቂቃም በሲዳማ ቡና ግብ ክልል በእጅ በመነካቱ ተከትሎ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ሃብቱም ሽዋለም መቶ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

በርካታ ሙከራዎች በታዩበት ጨዋታ ሲዳማዎች በዳዊት ተፈራ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ በስሑል ሽረዎችም በያሳር ሙገርዋ ፣ ሃብታሙ ሽዋለም እና መድሃኔ ብርሃኔ ሶስት ለግብ የቀረበ ሙከራዎች አድርገዋል በተለይም ዲድየ ሌብሬ አሻምቶት መድሃኔ ብርሃኔ በግምባሩ ያደረገው ሙከራ እና ሃብታሙ ሽዋለም በሳጥን ውስጥ መቶ መሳይ አያኖ በቀላሉ ያዳነው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በሃያኛው ደቂቃም በስሑል ሽረዎች ሳጥም በተሰራው ጥፋት ተከትሎ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ አስቆጥሮ ቡድኑ ጨዋታውን እየመራ ወደ እረፍት እንዲያመራ አስችሏል።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የጨዋታ ፍሰት የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ስሑል ሽረዎች በርካታ ለውጦች አድርገው ነበር የተመለሱት።
ሁለተኛው አጋማሽ በጥሩ መነቃቃት የጀመሩት ስሑል ሽረዎች ሙከራ ለማድረግም ቀዳሚ ነበሩ። ዓብዱልለጢፍ የግብ ጠባቂው መውጣት ተከትሎ ከረጅም ርቀት የመታው ኳስ ለጥቂት ወጥቷል። ሽረዎች ከሙከራው በኃም በበረከት ተሰማ ሁለት ጥሩ ሙከራዎች አድርገው ነበር በተለይም ተከላካዮ ከመአዝን የተሻገረው ኳስ መቶ የግቡን ቋሚ የመለሰበት ኳስ ቡድኑ አቻ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር።

በጨዋታው የተጋጣምያቸው የመከላከል ስህተቶች ተጠቅመው በርካታ ያለቀላቸው ዕድሎች ያመከኑት ሲዳማዎች በሰባ አንደኛው ደቂቃ ጥረታቸው ሰምሮ ግብ ጠባቂው ኳስ ለማራቅ በሰራው ስህተት በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። ወንድወሰን አሸናፊ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ወጥቶ ለማራቅ በሰራው ስህተት ነበር አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ከርቀት ግብ ያስቆጠረው።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩትም ይገዙ ቦጋለ ከቦታቸው ርቀው ሲከላከሉ የነበሩት የስሑል ሽረ ተከላካዮች በሰሩት የአቋቋም ስህተት ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር የቡድኑ የጎል መጠን ወደ አራት አድርሶ ጨዋታው ተጠናቋል።

ይሄን ተከትሎም ሲዳማ ቡናዎች ምድባቸው በበላይነት አጠናቀው በፍፃሜው ከወላይታ ድቻ ጋር መገናኘታቸው አረጋግጠዋል። የጨዋታው ኮከብም የሲዳማ ቡናው የመስመር አጥቂ ሃብታሙ ገዛኸኝ ሆኖ ተሸልሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ