ዐፄዎቹ የአሸናፊዎች አሸናፊ ክብርን ተቀዳጁ

ከቀናት ሽግሽግ በኃላ ዛሬ በአዲስአበባ ስታዲየም በተካሄደው የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለድሎቹ ፋሲል ከተማ የሊጉን ሻምፒየን መቐለ 70 እንደርታን 1ለ0 በማሸነፍ ክብሩን ተቀዳጅተዋል።

ከሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መጀመር በፊት በቅርቡ በምስረታ ላይ የሚገኘው ከኢትዮጵያ ደጋፊዎች ጥምረት የተወከሉ ደጋፊዎች በሁለት ተከፍለው የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል።

መቐለዎች ከተለመደው መለያ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር መለያን ለብሰው ወደ ጨዋታ በገቡበት ጨዋታ ፋሲሎች በሁለቱም አጋማሾች የተሻሉ ነበሩ ፤ መቐለዎች እጅግ ደካማ በነበሩበት ጨዋታ የዐምና ክብራቸውን ለማስከበር ከፍተኛ ቀሪ የቤት ስራ እንዳለባቸው ያሳየ ጨዋታ ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለት ፋሲሎች ያገኟቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም በ5ኛውና በ25ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ያገኛቸውና ፊሊፕ ኦቮኖ በአስደናቂ ሁኔታ ያዳነበት ሁለት አጋጣሚዎች በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበሩ።

በቅጣት ምክንያት አዲሱ ፈራሚያቸውን ኦኪኪ ኦፎላቢን በዛሬው ጨዋታ መጠቀም ያልቻሉት መቐለዎች ያለ ተፈጥሮአዊ 9 ቁጥር ተጫዋች ጨዋታውን መጀመራቸው ፊት ላይ ያስፈልጋቸው የነበረውን አካባቢያዊ ተፅዕኖ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ39ኛው ደቂቃ የፋሲል ከተማው የቀኝ መስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን ባጋጠመው ጉዳት በሰኢድ ሁሴን ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ኤፍሬም አሻሞ በ32ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ወደ ግብ በላካት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት መቀለዎች በደቂቃዎች ልዩነት አሸናፊ ሀፍቱ ድንገት ፋሲል ሳጥን ውስጥ ገብቶ የሞከራትና ሳሚኪ ያዳነበት ኳስ በጨዋታው መቀለዎች ያደረጓት ብቸኛ ጠንካራ ሙከራ ነበረች።

በመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ 20 ደቂቃች በተለይ ፋሲል ከተማ በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ አደገኛ ሁኔታዎች ላይ ኳሶችን በተደጋጋሚ ቢነጠቁሙ ምስጋና ለደካማው የመቐለ የማጥቃት ሽግሽር ይሆንና ዋጋ ከመክፈል ድነዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ ፋሲሎች በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉ ነበሩ፤ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ የመታትና ኦቮኖ ባዳነበት ኳስ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ፋሲሎች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

በአንፃሩ መቀየቐለዎች በመከላከሉ ረገድ በግለሰብ ደረጃ ከሚነሱ ጥንካሬዎች ውጭ ከወገብ በላይ የተሰለፉት ተጫዋቾች እጅግ ደካማ እንቅስቃሴን አሳይተዋል።

ጥረታቸው በስተመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ በ74ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ደገፍ በማድረግ አስቆጥሮ ቡድኑን ባለድል ማድረግ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ዋንጫውን ለፋሲል ከተማው አምበል ያሬድ ባየህ አስረክበዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ