ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የፕሪምየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች መካከል ለሊጉ እንግዳ የሆነው ወልቂጤን ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኘው ጨዋታን እንዲህ ተመልክተነዋል።

ፕሪምየር ሊጉን ለመጀመርያ ጊዜ የተቀላቀለው ወልቂጤ ከተማ የሊጉ ልምድ ያላቸውን ጨምሮ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ በማስፈረም የፕሪምየር ሊግ ፈተናውን ለመጀመር ተዘጋጅቷል። ቡድኑ የሚጠቀምበት የወልቂጤ ስታዲየምን ለሊጉ ብቁ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ በመሆኑ በጊዜያዊነት በሚጠቀምበት የባቱው ሼር ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ክለቡ በክረምቱ ካደረገው የዝውውር እንቅስቃሴ፣ ከአሰልጣኙ ተመራጭ አቀራረብ እና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከነበረው አጨዋወት በመነሳት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በነገው ጨዋታም አሰልጣኝ ደግአረግ ተመራጭ አጨዋወታቸውን ለመተግበር የሚያግዟቸውን በማጥቃት ላይ የተመሰረቱ ተጫዋቾችን እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል። በነገው ጨዋታ የሚገጥመው ቅዱስ ጊዮርጊስ በላይኛው የሜዳ ክፍል ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ቡድኖች የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ከኋላ እንዳይጀምሩ የሚያደርጉበት መንገድ ለወልቂጤ ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆን ይገመታል።

ቡድኑ በነገው ጨዋታ የመስመር አጥቂው ጫላ ተሺታ እና ተከላካዩ መሐመድ ሻፊን በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም።

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን በማንሳት በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ያጡትን የሊግ ክብር የማስመለስ አላማ አንግበው የውድድር ዘመኑን ይጀምራሉ። ቡድኑ ጠንካራ እና በአማራጮች የተሞላ የቡድን ስብስብ የያዘ ሲሆን ጥቂት ዝውውሮችን በማከል ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርጂዬን ቀጥረዋል።

በከተማው ዋንጫ ላይ የተመለከትነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደከዚህ ቀደሞቹ ዓመታት ሁሉ የኋላ መስመሩ የተረጋጋ እና የግብ እድል ለመፍጠር ክፍተት የማይሰጥ ሲሆን ከሌሎች ዓመታት በአንፃራዊነት በማጥቃት እንቅስቃሴ እና የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድ መሻሻል አሳይቷል። በቡድኑ ከወገብ በላይ የሚገኙ ተጫዋቾች የተጋጣሚን (በተለይም በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ቡድን) የኋላ መስመር ላይ ጫና በመፍጠር ስህተት እንዲፈጥር የሚያሳዩት ትጋት በመልካም ጎኑ የሚነሳ ነው። በተጨማሪም ቡድኑ ኳስ በሚያጣበት ወቅት በፍጥነት ኳስ ለማስመለስ የሚያደርገው ጥረት እንዲሁም ቡድኖች ወደ መከላከል አደረጃጀት ሳይገቡ በፍጥነት ወደ ጎል ክልል በመግባት አደጋ ሲፈጥሩ በተደጋጋሚ መስተዋሉ ቡድኑ ለተጋጣሚ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርገዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ገና በውድድር ዓመቱ ጅማሮ በጉዳት ታምሷል። አስቻለዉ ታመነ፣ መሀሪ መና፣ ለአለም ብርሀኑ፣ ፓትሪክ ማታሲ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ሳላሀዲን በርጊቾ፣ አሜ መሀመድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሳላሀዲን ሰዒድም የነገው ጨዋታ ላይ የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– የነገው ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነት ነው።

– በአዲስ አባበ ከተማ ዋንጫ በአንድ ምድብ ተደልድለው የነበሩት ሁለቱ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

መሐመድ ዐወል – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሴ – አቤኔዘር ኦቴ

አሳሪ አልመሐዲ – ኤፍሬም ዘካርያስ – አብዱልከሪም ወርቁ

ሄኖክ አወቀ – ጃኮ አራፋት – አህመድ ሁሴን

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ባህሩ ነጋሽ

አብዱልከሪም መሐመድ – ምንተስኖት አዳነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ሄኖክ አዱኛ

ሙሉዓለም መስፍን – የአብስራ ተስፋዬ

ጋዲሳ መብራቴ – አቤል ያለው – አቡበከር ሳኒ

ዛቦ ቴጉይ


© ሶከር ኢትዮጵያ