ሪፖርት | ወልዋሎዎች ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል

ወልዋሎ በካርሎስ ዳምጠው እና ሰመረ ሃፍታይ ግቦች ወላይታ ድቻን 2-1 አሸንፏል።

ሁለቱ በሊጉ አናት የሚገኙትን ክለቦች ባገናኘው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ከባለፈው ሳምንት ቡድናቸው ኢታሙና ኬይሙኔ እና ጁንያስ ናንጋጂቦን በሰመረ ሃፍታይ እና ራምኬል ሎክ ተክተው ሲገቡ ወላይታ ድቻዎችም ባዬ ገዛኸኝ እና እዮብ ዓለማየሁን በዳንኤል ዳዊት እና ፀጋዬ አበራ ተክተው ገብተዋል።

በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ የተካሄደው የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን ማራኪ እንቅስቃሴ ባይታይበትም በርካታ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። ጎል ያስተናገደውም ገና በሦስተኛ ደቂቃ ላይ ነበር። በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኘው ካርሎስ ዳምጠው በሳጥኑ ቀኝ ጠርዝ ያገኛትን ኳስ በግራ እግሩ አክርሮ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱት ወልዋሎዎች ከግቡ በኃላም በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ሄኖክ መርሹ ከርቀት አክርሮ መቷት ለጥቂት የወጣችው ሙከራ እና ካርሎስ ዳምጠው በሁለት አጋጣሙዎች ሞክሯቸው መክብብ ደገፉ ያወጣቸው ኳሶች ይጠቀሳሉ።

ለግማሽ ሰዓት በነበረው እንቅስቃሴ ይህ ነው የሚባል ንፁህ የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩት የጦና ንቦች ሰሠላሳኛው ደቂቃ በኃላ የተሻለ ተንቀሳቅሰው የግብ ዕድሎችም ፈጥረዋል። ከነዚህም ተስፋዬ አለባቸው በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት ያደረጋቸው ጥሩ ሙከራዎች ወላይታ ድቻዎች አቻ ለማድረግ ተቃርበው ነበር።
በ38ማው ደቂቃም ፀጋዬ ብርሃኑ ከፀጋዬ አበራ በጥሩ ሁኔታ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች ከተጋጠሚያቸው በቁጥር የተሻለ የግብ ሙከራዎች ያደረጉበት ነበር። በተለይም ካርሎስ ዳምጠው ከቅጣት ምት መቷት ቋሚው ገጭታ የወጣች ኳስ፣ በተመሳሳይ ካርሎስ ከቅጣት ምት መቷት መክብብ ደገፉ ያዳናት ኳስ እና ሰመረ ሃፍታይ ከርቀት መቷት መክብብ ደገፉ እንደምንም ያወጣት ኳስ እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ከነዚህ ውጭም ራምኬል ሎክ ተጠቃሽ ሙከራ አድርጓል።

በሀምሳ ዘጠነኛው ደቂቃ ምስጋናው ወልደዮሐንስ ከመስመር አሻምቷት በተጫዋቾች ተደርባ የመጣችው ኳስ ወጣቱ ሰመረ ሀፍታይ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ በኋላ አቻ ለመሆን ተጭነው የተጫወቱት ወላይታ ድቻዎች በሁለት አጋጣሚዎች የሚስቆጩ ወርቃማ ዕድሎች አምክነዋል።

ውጤቱ በዚ መጠናቀቁ ተከትሎ ወልዋሎዎች ነጥባቸው ስድስት በማድረስ ሊጉን ሲመሩ ወላይታ ድቻዎች በሶስት ነጥብ ባሉበት ረግተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ