ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ወልቂጤ ከተማ

በአምስተኛው ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ሶዶ ላይ የሚደረገው የወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በመክፈቻው ሳምንት ድል ካስመዘገበ በኋላ ሽንፈት እና ተከታታይ አቻዎች ያስመዘገበው ወላይታ ድቻ ወደ ድል በመመለስ ለማንሰራራት የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ከፊት በብቸኝነት የሚሰለፈው ባዬ ገዛኸንን ማዕከል ያደረገው የወላይታ ድቻ የማጥቃት እንቅስቃሴ ከብቸኛው የተከላካይ አማካይ ፊት ለፊት የሚገኙት አራት አማካዮች ብቃት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል። በተለይም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረገው ሽግግር ላይ የሚኖራቸው ስኬታማነት ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወሳኝ ነው።

የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን ለኳስ ቁጥጥር ቁጥጥር እና ለማጥቃት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ባለፉት ጨዋታዎች ያሳየ ቢሆንም የተሳኩ ቅብብሎችን በማጥቃት ወረዳ ላይ ማድረግ እና በርካታ የጎል እድል መፍጠር ላይ ያለበትን ድክመት ማሻሻል ይጠበቅበታል።

ወላይታ ድቻ የመስመር ተጫዋቹ ቸርነት ጉግሳን ከቅጣት መልስ ሲጠቀም ተስፋዬ አለባቸው እና መክብብ ደገፉም ከጉዳት አገግመው ለነገው ጨዋታ ብቁ ሆነዋል። ያሬድ ዳዊት፣ ነጋሽ ታደሰ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ያስተናገደው በረከት ወልዴ አሁንም ለጨዋታው አይደርሱም፡፡

ባለፈው ሳምንት በሰበታ ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ወልቂጤ ከተማ ወደ ድል በመመለስ ደረጃውን ለማሻሻል አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

ጥቂት ጎሎች (1) ካስቆጠሩ የሊጉ ቡድኖች አንዱ የሆነው ወልቂጤ ከተማ በግልፅ የሚታይ የማጥቃት ችግር ይታይበታል። ብዙም የጎል እድል የማይፈጥረው ቡድኑ ስኬታማ ካልሆኑ ረጃጅም ኳሶች ባሻገር ሁነኛ የማጥቃት ስልት ማግኘት የአሰልጣኙ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።

ቡድኑ ከያዘው ስብስብ እና ከአሰልጣኙ ባህርይ በመነሳት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት እንቅስቃሴን ምርጫው እንደሚያደርግ ቢጠበቅም በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን መተግበር አልቻለም። በነገው ጨዋታም ከሜዳው አለመመቸት ጋር ተዳምሮ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እንደተስተዋለው አጥቂው ጃኮ አራፋትን ማዕከል ያደረጉ ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶችን እንደሚጠቀሙ ይጠበቃል። በሜዳው ቁመት እና ስፋት ጥሩ መመጣጠን ካለው እንዲሁም በርካታ አማካዮችን ከሚጠቀመው ድቻ የበላይነቱን ለመውሰድ ከኳስ ጋር ጥሩ የሆኑ አማካዮችን ሊጠቀም እንደሚችል ይገመታል።

ወልቂጤ አሁንም ቶማስ ስምረቱን በጉዳት የማያሰልፍ ሲሆን የመስመር ተከላካዩ አዳነ አባይነህ እና መሐመድ ሻፊ (ቀላል ጉዳት) በጉዳት የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጥሯል። ኤፍሬም ዘካርያስ ደግሞ ከቅጣት የተመለሰ ተጫዋች ነው።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉመጀመርያ ግንኙነታቸው ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

መኳንንት አሸናፊ

ፀጋዬ አበራ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – ይግረማቸው ተስፋዬ

ተስፋዬ አለባቸው

ቸርነት ጉግሳ – ዘላለም ኢያሱ – እድሪስ ሰዒድ – ፀጋዬ ብርሀኑ

ባዬ ገዛኸኝ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ይበልጣል ሽባባው – ዳግም ንጉሴ – ዐወል መሐመድ – አቤኔዘር ኦቴ

ፍፁም ተፈሪ – በረከት ጥጋቡ – ኤፍሬም ዘካርያስ

ጫላ ተሺታ – ጃኮ አራፋት – አብዱልከሪም ወርቁ


© ሶከር ኢትዮጵያ