ሪፖርት| ሀዋሳ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል

በሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል፡፡

ሀዋሳ በስድስተኛው ሳምንት ወደ መቐለ ተጉዞ ከወልዋሎ አንድ ነጥብ ይዞ ከተመለሰበት የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ውስጥ ፀጋአብ ዮሐንስን በአክሊሉ ተፈራ ብቻ በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ መቐለን በአዲስ አበባ ስታዲየም ረተው የመጡት ፈረሰኞቹ አንድም ተጫዋች ከባለፈው ጨዋታ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

ፌድራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ሳይቸገሩ ዘጠና ደቂቃውን መርተው በፈፀሙበት በዚህ ጨዋታ ከጨዋታው ይልቅ እንደ ቡድን ሁለቱም ክለቦች በእንቅስቃሴ ብልጫን ለመውሰድ ከመታተር ይልቅ ተጫዋቾች በግላቸው ቀዳዳ እየፈለጉ ከርቀት ለመምማት የሚሞክሩበትን ሂደት በግልፅ ያየንበት ነበር። ከባለሜዳው ሀዋሳ ከተማዎች በተቃራኒው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሙከራ ረገድ የተሻሉ መሆናቸውን ባደረጉት በርካታ ሙከራዎች ማስተዋል የቻልን ሲሆን ካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ኢኖህ ድንቅ ብቃት ግን ሀይቆቹ መረባቸውን ላለማስደፈራቸው ተጠቃሹ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎችም ጥቂት አጋጣሚዎች ለመፍጠር በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉበት ቢሆንም እንደ ሀዋሳው ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ሁሉ የባህሩ ነጋሽ የግል ብቃቱም ግብ ሊሆኑ የተቀራቡትን ጥቂት አጋጣሚዎች በማምከኑም የተዋጣለት ሆኗል፡፡

የሁለቱንም ቡድኖች እንቅስቃሴ ይህ ነው ለማለት ብንቸገረም የግብ ሙከራን ለማየት ግን ብዙ ደቂቃዎች አላስፈለጉንም፡፡ 2ኛው ደቂቃ የሀዋሳው ተከላካይ መሳይ ፓውሎስን ስህተት የጠበቀው ጋዲሳ መብራቴ በፍጥነት ኳሱ እግሩ ከገባ በኃላ ለጌታነህ ሰቶት አጥቂው አክርሮ ወደ ግብ ሲመታው ቢሊንጌ እንደምንም አውጥቷታል፡፡18ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል ደስታ ደሙን በግሩም ሁኔታ ያለፈው መስፍን ታፈሰ ኳሷን ይዞ ሳጥኑ ጠርዝ መጠጋት ከቻለ በኃላ በቀጥታ መቶ ባህሩ አውጥቶበታል፡፡ ኳስ ቅብብል ላይ ትኩረት ለማድረግ ቢያስቡም አላዋጣ ሲላቸው ረጃጅም ኳሶች ላይ ትኩረታቸውን በፍጥነት የለወጡት ፈረሰኞቹ በዚህ ሂደት ጋዲሳ መብራቴ በረጅሙ የጣለለትን አቤል ያለው ተቆጣጥሮ ነፃ ቦታ ላይ ቆሞ ለነበረው ጌታነህ አጥቂውም በፍጥነት ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራን አድርጎ ቢሊንጌ አሁንም በአስደናቂ ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡

ባለሜዳዎች ከሀያ አምስተኛው ደቂቃ በኃላ ኳስን ይዞ ወደ መጫወቱ ፊታቸውን ማዞር ቢችሉም የቅብብሎሽ ስህተት ግን ታይቶባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአማካይ ስፍራው ላይ የተረጋጋ እኛ የበሰለ የጨዋታ ሂደትን ሲከተል የነበረው ሄኖክ ድልቢ ጥሩ ጥሩ ኳሶች ወደ አጥቂዎቹ ቶሎ ቶሎ ሲያሻግር ተመልክተናል፡፡ በዚህም ሂደት 26ኛው ደቂቃ ሄኖክ በረጅሙ የሰጠውን መስፍን ተቆጣጥሮት እንደ መጀመሪያ ሙከራው አክርሮ መትቶ ባህሩ አሁንም አውጥቶበታል፡፡ 29ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ መስመር ተከላካዩ አክሊሉ ተፈራ እየገፋ መቶ ግብ ክልል ላይ ሲደርስ አክርሮ መቶ የባህሩ ነጋሽ ድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን ተርፋለች፡፡

37ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ፈረሰኞቹ ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል በፍጥነት መተው ጋዲሳ እግር ገብታ ተጫዋቹ እንደ ጌታነት አይነት ተመሳሳይ ሙከራን አድርጎ ቢሊንጌ በአስገራሚ መልኩ አድኖበታል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በቀኝ በኩል የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል በግሉ ሲረብሽ የነበረው መስፍን ታፈሰ ተከላካዮቹን በማለፍ ጠንካራ ሙከራን አድርጎ የግቡ ቀኝ ቋሚ ብረት መልሶታል ምናልባትም ሀዋሳን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ የምታደርግ የነበረች ቢሆንም ከመረብ ሳታርፍ ወጥታለች፡፡

ከእረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ የማጥቃት ኃይላቸውን ይዘው የገቡበት በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማዎች መስፍን ታፈሰን በጉዳት ካጡ በኃላ ለማጥቃት የነበራቸው ፍላጎት ቀዝቀዝ ብሎ የታየበት ነበረ፡፡ ፈረሰኞቹ በርካታ አጋጣሚዎች ቢያገኙም ግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ኢኖህ ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል፡፡ 49ኛው ደቂቃ ላይ ሳላሀዲን ሰዒድ ብልጠቱን ተጠቅሞ ለጌታነህ የሰጠውን አጥቂው አክርሮ መቶ ቢሊንጌ አሁንም አውጥቶበታል፡፡ በአንፃሩ ሀዋሳዎች ሄኖክ ድልቢ የቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል ክፍተት እያየ ከርቀት ከሚመታቸው ኳሶች ውጪ የጎሉ ግልፅ ዕድሎችን አላየንም፡፡ 78ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ሰቶ ሳላሀዲን ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በግሩም ሁኔታ ከግቡ ጠርዝ ላይ አውጥቷታል፡፡

በእንቅስቃሴ ረገድ ብዙም ባልነበረው በዚህ አጋማሽ አሁንም ፈረሰኞቹ በጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች ቢያገኙም የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ኢኖህ አድኖባቸዋል፡፡ በተለይ 90+1 ተቀይሮ የገባው አቤል እንዳለ ለአቤል ያለው ሰጥቶት አቤልም ሲመታው ቢሊንጌ ያዳነበት ምናልባትም እንግዳዎቹን አሸናፊ ለማድረግ በስተመጨረሻ የተቃረበች ብትመስልም መቆጠር ሳይችል፡፡ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ