“ወደ ስሑል ሽረ ለመምጣት የወሰንኩት በዋነኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ላለመራቅ ነው” ምንተስኖት አሎ

በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ግቡን ያላስደፈረው ምንተስኖት አሎ ስለ ወቅታዊ አቋሙ ይናገራል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ እግሩ ኳሱ ብቅ ካሉት ተስፈኛ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ነው። በሰበታ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ መጫወት የቻለው ምንተስኖት አሎ በተለይም ባህር ዳር ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ ጉልህ ድርሻ ነበረው።

ባለፈው ዓመት በዋናው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መጫወት የጀመረው ይህ ግብ ጠባቂ በዚህ ዓመት ወደ ስሑል ሽረ ተዘዋውሮ ጥሩ ብቃት በማሳየት ይገኛል። በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ጥሩ ብቃቱን ለማውጣት ተቸግሮ የነበረው ምንተስኖት አሎ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ወደ ጥሩ ብቃቱ ተመልሶ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሏል።

ተጫዋቹ ስለ ወቅታዊ ብቃቱ፣ ስለ ቀጣይ እቅዱ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

👉 ስለ ወቅታዊ አቋሙ

ቡድናችን አዲስ ነው። ማለቴ በዚህ ዓመት ነው የተዋቀረው። በበርካታ አዳዲስ እና ወጣት ተጫዋቾች የተገነባ ቡድን ነው ያለን። በዚህም መጀመርያ አከባቢ ትንሽ መንገራገጮች ነበሩ። ከዛ በኃላ ብዙ ግን መሻሻሎች አሳይተናል። የሚሰጠኝን ልምምድ በአግባቡ እየተከታተልኩ በጥሩ ብቃት ላይ እገኛለው። ከዚህ ባለፈም ቡድናችን በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች የነበሩበትን የመከላከል ክፍተቶች ለማሻሻል ከቡድን ጓደኞቼ ጋር ጠንክረን በመስራት ለተከታታይ አራት ጨዋታዎች ግባችንን አላስደፈርንም። በግሌም ግቦችን እንዳይቆጠሩ በመከላከል እና የቡድን ጓደኞቼን ከኋላ ሆኜ በመምራት የበኩሌን እየተወጣው እገኛለው።

👉 በተከታታይ ጨዋታዎች ግቡ አለማስደፈሩ የፈጠረለት ስሜት

ይህ ነገር እንደ ቡድን ነው ያሳካነው ሁሉም የቡድናችን አባል ጠንክሮ በመስራቱ የመጣ መሻሻል ነው። በግሌ ግን በጣም ደስ ብሎኛል። በቀጣይም ከዚህ የተሻለ ነገር እንድሰራ ጥሩ መነሳሻ ነው ሚሆነኝ።

👉 ቡድኑ ስላሳየው መሻሻል

አዎ በውድድሩ መጀመርያ ችግሮች ነበሩ። እንደ ቡድንም በግልም። ቅድም እንዳልኩት ቡድናችን አዲስ የተዋቀረ ቡድን እንደመሆኑና በቅድመ ውድድር ላይ በቂ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች አለማድረጉ ክፍተቶች ፈጥሮብናል። በሒደት ግን አሰልጣኞቻችን በሰሩት ሥራ ቡድናችን ተዋህዶ አሁን በጥሩ ብቃት ላይ ይገኛል።

👉 ስለ ቀጣይ እቅዱ

ወደ ስሑል ሽረ ለመምጣት የወሰንኩት በዋነኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ላለመራቅ ነው። በጥቅማ ጥቅም ደረጃ የተሻሉ ጥያቄዎች ቀርበውልኝ ነበር። ሆኖም የመጫወት ፍላጎት ስላለኝ እና ከብሄራዊ ቡድን ላለመራቅ የተሻሉ ነገሮች ትቼ ነው ወደ ሽረ የመጣሁት። በቀጣይም ከፈጣሪ ጋር ክለቤም ከብሄራዊ ቡድኔም በተሻለ ብቃት ለማገልገል ጠንክሬ እሰራለው።

በሊጋችን የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ይበዛሉ። ይህም በሀገር በቀለ ግብ ጠባቂዎች እድገት ላይ ጥሩ ያልሆነ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ