ሪፖርት | ስሑል ሽረ እና ጅማ አባ ጅፋር ነጥብ ተጋሩ

በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባጅፋርን ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ነጥብ ጥለዋል።

በሽረ በኩል ፋሲል ከነማ ካሸነፈው ስብስብ ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ በወንድወሰን አሸናፊ ተክተው ሲገቡ ጅማ አባጅፋሮች በሜዳው በወላይታ ድቻ ሽንፈት ከደረሰበት ስብስብ መሐመድ ሙንታሪ፣ ሱራፌል ዐወል፣ ኤርሚያስ ኃይሉ እና መሐመድ ያኩቡን በማሳረፍ ሰዒድ ሀብታሙ፣ አብርሀም ታምራት፣ ኤፍሬም ጌታቸው እና አምረላ ደልታታ ተተክተዋል ገብተዋል።

ብዙም ሳቢ ባልነበረው የመጀመርያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ ጨዋታ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። ዐወት ገብረሚካኤል እና ዲዲዬ ለብሪ በተሰለፉበት የቀኝ መስመር ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት ባለሜዳዎቹ በተለይም ጫና በፈጠሩባቸው የመጀመርያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል።

ከነዚህም በመጀመርያው ደቂቃ ሳሊፍ ፎፋና ዲዲዬ ለብሪ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ እና አብዱልለጢፍ መሐመድ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቶ ሰዒድ ሀብታሙ እንደምንም ያወጣው ኳስ ይጠቀሳሉ።
ረመዳን የሱፍ ሰይድ ሀብታሙ የተፋውን ኳስ መቶ የግቡን ቋሚ ለትማ የወጣችው ኳስም ስሑል ሽረን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

በአጋማሹ ዘግይተው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ የገቡት ጅማ አባ ጅፋሮችም በተለይም በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ኤልያስ አሕመድ በተጋጣሚ ሳጥን ያገኛትን ኳስ መትቶ ወንድወሰን አሸናፊ የመለሰለት ኳስ እና ሄኖክ ገምቴሳ ኤልያስ አሕመድ በጥሩ ብቃት ያሾለኮለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት እጅግ አስቆጪ ሙከራ ጅማ አባጅፋርን ቀዳሚ ለማድረግ የምታስችል ነበረች። ብዙም ሳይቆይ በ44ኛው ደቂቃም ኤልያስ አሕመድ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በቁጥር ያነሱ ሙከራዎች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በብዙ ረገድ የወረደ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ነበር።

በዚህም ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ንፁህ የግብ ዕድል የፈጠሩት በተወሰኑ አጋጣሚዎች ቢሆንም ጎል የተስተናገደው ገና በመጀመርያው ደቂቃ ነበር። በ46ኛው ደቂቃ አብዱለጢፍ መሐመድ ከመስመር አሻምቷት ስዒድ ሀብታሙ ደርሶ ካዳናት በኃላ ኳሷ አምልጣው በቅርብ ርቀት የነበረው ዲዲዬ ለብሪ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ስሑል ሽረዎች ከግቡ በኋላም ወደ መሪነት ለመሸጋገር ያለሙ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም ሀብታሙ ሽዋለም በሳጥን ውስጥ አታሎ በማለፍ መቷት ሰዒድ ሀብታሙ ያዳናት እንዲሁም ዲዲዬ ለብሪ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ረመዳን የሱፍ ከቅርብ ርቀት አግኝቶ ከግቡ በላይ የላከው ኳስ አስቆጪ ሙከራ ነበር። ባለሜዳዎቹ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጪ በኃይለአብ ኃይለሥላሴ ሙከራዎች አድርገው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ኤልያስ አሕመድ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጭ እንደ ቡድን ማጥቃት ያልቻሉት ጅማ አባጅፋሮች በአጋማሹ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ውጤቱ በዚህ መጠናቀቁ ተከትሎ ስሑል ሽረዎች ከመሪው ጋር የነበራቸው የነጥብ ልዩነት ይበልጥ የማጥበብ ዕድላቸውን ቢያመክኑም በጊዜያዊነት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። ጅማ አባጅፋሮች ነጥባቸው ወደ 11 ከፍ ቢያደርጉም ወደ 12ኛ ደረጃ ዝቅ ሊሉ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ