ሪፖርት | የጣና ሞገዶች የዓመቱን አጋማሽ በድል አጠናቀዋል

በ3ኛ ቀን የ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ስሑል ሽረን ጋብዞ 1-0 አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሶዶ አምርተው አንድ ለምንም ከተረቱበት የመጀመርያ 11 ሚኪያስ ግርማን እና ደረጄ መንግስቱን በሳላምላክ ተገኝ እና ፍፁም ዓለሙ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ ስሑል ሽረዎች ደግሞ በሜዳቸው ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ስብስብ ክብሮም ፍሰሃ፣ ክፍሎም ገ/ህይወት እና ሀፍታሙ ሸዋለምን በአዳማ ማሳላቺ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና መድሃኔ ብርሃኑ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማህበር ለቀድሞ ግብ ጠባቂያቸው ምንተስኖት አሎ ምስሉ ያረፈበት ፎቶ በፍሬም አሰርተው በስጦታ መልክ አበርክተውለታል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል በነበረ ፍጥነት የተሞላበት እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታው ገና በ3ኛው ደቂቃ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃ ስሑል ሽረዎች በያስር ሙገርዋ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። ገና በጅማሮ በዚህ የግብ ማግባት ሙከራ ብቻ ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል መድረስ ያላቆሙት ሽረዎች ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሌላ ጥቃት በመድሀኔ ብርሃኔ አማካኝነት ሰንዝረዋል።

በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተሽለው የታዩት ባህር ዳር ከተማዎች ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ስሑል ሽረዎች የግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውሏል። በ14ኛው ደቂቃም ፍቃዱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ዳንኤል አሻምሮት በተሞከረ ጥሩ ሙከራ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። ለዚህ የቅጣት ምት መገኘት ምክንያት የሆነው ፍቃዱ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ጥሩ ኳስ ከቀኝ መስመር ወደ መሃል አሻግሮ ፍፁም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በተለይ በቆሙ ኳሶች የሽረን መረብ ለመጎብኘት የጣሩት ባለሜዳዎቹ በ20ኛው ደቂቃ ሌላ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ የተገኘን የመዓዘን ምት ግዙፉ የተከላካይ መስመር ተጨዋች አቤል በግንባሩ ሞክሮ ወጥቶበታል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ ከቆመ ኳስ በግርማ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝሮ መክኖበታል። እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ሽረዎች መልሶ ማጥቃትን እና የአግድሞች ረጃጅም ኳሶችን በማዘውተር ጨዋታውን ቀጥለዋል። በዚህም ቡድኑ በ26ኛው ደቂቃ በነፃነት አማካኝነት ጥሩ ኳስ ወደ ጎል መትቶ ወጥቶበታል።

የቆሙ ኳሶችን መጠቀም የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በ42ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃ ሳሙኤል ላይ የተሰራን ጣፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ግርማ አሻምቶት ፍፁም በግንባሩ አስቆጥሯል።

ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ እያስቀጠሉ እያለ ግብ ያስተናገዱት ሽረዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ተገባዶ በጭማሪው ደቂቃ የአቻነት ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ በግራ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው መሐመድ ለጢፍ ከመዓዘን የተቀበለውን ኳስ አክርሮ በመምታት ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። ነገር ግን ሙከራው ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ አጋማሹ በባለሜዳዎቹ መሪነት ተጠናቋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ ተሟሙቆ የጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ በ48ኛው እና በ51ኛው ደቂቃ ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች አስተናግዷል። በቅድሚያም ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች በ48ኛው ደቂቃ ሳሙኤል በግራ መስመር አሻምቶት ስንታየሁ ባመከነው ሙከራ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ ሽረዎች ደግሞ በ51ኛው ደቂቃ በተገኘ የባህር ዳር ከተማ ተጨዋቾች የቅብብል ስህተት ጥሩ ሙከራ አድርገዋል።

በአንፃራዊነት ተሻሽለው የቀረቡት ስሑል ሽረዎች ፈጣን ሽግግሮችን እና ረጃጅም ኳሶችን በአላማ በማከናወን ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። በተለይ ቡድኑ በግራ መስመር በኩል አጋድሎ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክሯል። በ69ኛው ደቂቃም ቡድኑ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ደርሶ በሳሊፍ ፎፋና አማካኝነት የሞከረው ሙከራ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል። በተቃራኒው ከወገብ በላይ ያሉት ተጨዋቾች ተዳክመውበት የታየው ባህር ዳር ከተማ የአማካይ መስመር ተጨዋቾችን እና የተከላካይ መስመር ተጨዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ጥንቃቄን ለመምረጥ ሞክሯል።

ከተቻለ ሶስት ነጥብ ካልተቻለ አንድ ነጥብ ከጨዋታው ይዞ ለመውጣት ጥረቶችን አጠናክረው የቀጠሉት ሽረዎች በ71ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምት ድንቅ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ አጋማሽ የተወሰደባቸውን አንፃራዊ ብልጫ ለመቋቋም የጣሩት ባህር ዳሮች በ85ኛው ደቂቃ በአምበላቸው አማካኝነት ጥብቅ ኳስ ወደ ግብ መትተው መክኖባቸዋል።

የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አካላዊ ጉሽሚያዎች የበዙበት ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በባህር ዳር 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ 7ኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 23 ከፍ በማድረግ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተቃራኒው ከጨዋታው ሶስት ነጥብ አስረክበው የወጡት ስሑል ሽረዎች ከነበሩበት 6ኛ ደረጃ ወደ 8ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ