ድሬዳዋ ከተማ ሁለት የመቐለ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል

ባለፈው ዓመት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሱት የመስመር ተጫዋቹ ያሬድ ብርሀኑ እና ሁለገቡ ሄኖክ ኢሳይያስ ወደ ብርቱካናማዎቹን ለማቅናት ተቃርበዋል።

ከዚህ ቀደም በመቐለ 70 እንደርታ፣ ደደቢት እና ወልዲያ መጫወት የቻለው ፈጣኑ ያሬድ ብርሀኑ በተለይም ባለፈው ዓመት ቡድኑ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ተቀይሮ እየገባ ቡድኑን ማገልገሉ ሲታወስ በዚህ ዓመትም በተወሰኑ ጨዋታዎች በቋሚነት እና ተቀይሮ እየገባ ቡድኑን አገልግሏል። ከድሬዳዋ ጋር በቃል ደረጃ የተስማማው ያሬድ ብርሀኑ በቀጣይ ቀናት ከክለቡ ጋር በይፋ ይቀላቀላል ተብሎ ይገመታል። የመስመር አማካዩ በዘንድሮ ውድድር ዓመት 117 ደቂቃዎች ቀዩን ማልያ ለብሶ የተጫወተ ሲሆን በአምስት ጨዋታዎች ተሳትፎ አድርጓል።

ሌላው ብርቱካናማዎቹን ለመቀላቀል የተስማማው ሁለገቡ ሄኖክ ኢሳይያስ ነው። በአማካይነት እና በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ይህ ተጫዋች ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ወላይታ ድቻን ለቆ መቐለን በመቀላቀል በበርካታ ጨዋታዎች ቡድኑን ማገልገሉ ይታወሳል። ከደደቢት፣ ጅማ አባ ጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ጋር ሦስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ሄኖክ ኢሳይያስ በዚህ የውድድር ዓመት ሦስት ጨዋታዎች በቋሚነት በዘጠኝ ጨዋታዎች ተቀይሮ በመግባት በአጠቃላይ 399 ደቂቃዎች ቆይታ ማድረግ ችሏል።

ከዝውውር ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት ወደ ድሬዳዋ ለማምራት ተቃርቦ የነበረው እንዳለ ከበደ ዝውውር ሳይሳካ መቅረቱ ታውቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ