ወልቂጤ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀቀ

በትናትናው ዕለት ወደ ወልቂጤ ለማምራት ከስምምነት ደርሰው የነበሩት ተስፋዬ መላኩ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ዛሬ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ሀዋሳ ከተማን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ተቀላቅሎ የነበረው እና የአምስት ወራት ቀሪ ውል እየቀረው ከሰሞኑ በስምምነት የተለያየው ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ ወልቂጤ ከተማን በአንድ አመት ዛሬ ረፋድ ተቀላቅሏል፡፡ ቀዳሚ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውን በተለያየ ምክንያት በማጣት ላይ የነበሩት ደግአረግ ይግዛው በተስፋዬ ፊርማ ጥሩ አማራጭ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ሌላው ትናንት በቃል ደረጃ መስማማቱን ዘግበንላችሁ የነበረው ሳሙኤል ሳሊሶ በተመሳሳይ ፊርማውን ዛሬ አኑሯል። የመስመር ተጫዋቹ ከሳምንታት በፊት ከመቐለ ጋር በስምምነት መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን በጫላ ተሺታ ላይ መሰረት ላደረገው የመስመር አጨዋወት ጥሩ ግብዓት ይሆናል ተብሏል።

ወልቂጤ ከተማ እስካሁን በዝውውር መስኮቱ አራት ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

© ሶከር ኢትዮጵያ