ወልቂጤ ከተማ ከሁለት ተጫዋቾች ጋር ተለያየ

አማካዩ ፍፁም ተፈሪ እና ተከላካዩ ዐወል ከድር ከወልቂጤ ከተማ ጋር በስምምነት ተለያይተዋል።

ወላይታ ድቻን ለቆ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ወልቂጤ ከተማን ተቀላቅሎ የነበረው የቀድሞው የሀዋሳ፣ ሲዳማ፣ ባንክ፣ ጊዮርጊስ እና ደደቢት አማካይ ፍፁም ተፈሪ በከፊል ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ቡድኑን ያገለገለ ሲሆን ቀሪ ውል እያለው በስምምነት ከክለቡ ጋር ሊለያይ ችሏል።

ግዙፉ የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዐወል ከድር ከቡድኑ ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ ተጫዋች ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ አብረው ካደጉ ተጫዋቾች አንዱ ነበር። ተከላካዩ ዘንድሮ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ አድርጎ ቀሪ ውል እየቀረው ተለያይቷል።

ወልቂጤዎች በዚህ የዝውውር መስኮት እስካሁን ከስድስት ተጫዋቾች ጋር በመለያየት በምትኩ አምስት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ