ድሬዳዋ ከተማ አዲስ ረዳት አሰልጣኝ እና ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅ ሾመ

የድሬዳዋ ከተማ ቦርድ ፍአድ የሱፍን በረዳት አሰልጣኝነት ዳዊት ከድርን ደግሞ በጊዜያዊ ስራ አስኪያጅነት መሾሙን አስታውቋል።

የድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ የቦርድ አባላት ትላንት አመሻሽ ባካሄደው ስብሰባው በቅርቡ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ በማድረግ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለተሾመው ፍሰሀ ጥዑመልሳን ረዳት በማድረግ የሾመው ፉአድ የሱፍ በተጫዋችነት ዘመኑ ለድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ፣ ሀፍካት እና ምድር ባቡር የተጫወተ ሲሆን በአሰልጣኝነት ደግሞ በሀረር ቢራ (አሁን ሀረር ከተማ ) መስራቱን የክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ገልጿል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ከዚህ ባለፈ ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅም መድቧል፡፡ በቅርቡ ጊዜያዊ ስራ አስኪያጅ በመሆን ተመድቦ ለአጭር ጊዜ ያገለገለውን ፍፁም ክንድሼ ወደ ምክትል ቦታ ሲቀየር በቦታው ደግሞ ዳዊት ከድርን በጊዜያዊ ዋና ስራ አስኪያጅነት ሾሟል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ከትላንት በስቲያ የክለቡ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት በድሬዳዋ ከተማ ለሚገኘው ዳዊት የአረጋዊያን መርጃ ማኅበር በቦታው ድረስ በመሄድ ከሀያ ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የቀለብ እህልን በስጦታ አበርክቷል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ