የ2012 የኢትዮጵያ ሊጎች ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዙ ተደረገ

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የሊግ ውድድሮች ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝ ተደረገ። በተጨማሪም በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን በአህጉራዊ ውድድሮች የሚወክል ክለብ እንዳይኖር ተደርጓል።

በታህሳስ ወር በቻይና ሁቤይ ከተማ በተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ምክንያት በዓለም ላይ የሚደረጉ የሊግ ውድድሮች ቆመዋል። ሊጎችን የሚያስተዳድሩ አካላትም የሊጎቻቸውን ቀጣይ እጣ ፈንታ በማጤን ውሳኔዎችን እየወሰኑ ይገኛሉ። በሃገራችንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሊጉን ከሚያስተዳድረው የሊግ ካምፓኒ እና ከመንግስት አካላት ጋር ዛሬ ረፋድ በቴሌ ኮንፍረንስ ውይይት አከናውኖ የመጨረሻ ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም የ2012 የሊግ ውድድሮች ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸውን፣ ውድድሩ በመሰረዙም በየትኛውም ሊግ ሻምፒዮን እና ወራጅ የሌለ መሆኑን በተጨማሪም በቀጣይ ዓመት(2013) ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የሚወክል ክለብ አለመኖሩን አስታውቋል። ከውሳኔው ጎን ለጎን ክለቦች እስከ 2012 ኮንትራት ላላቸው ተጨዋቾች ተገቢ የደሞዝ ክፍያ እንዲከፍሉ አሳስቧል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ