ኢትዮጵያ ቡና ከተጫዋቾቹ ጋር ውይይት ሊያደርግ ነው

በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት የሊጉ ውድድር መቋረጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በአሁኑ ወቅት የሚገኝበት ሁኔታ እና የተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያን አስመልክቶ ውይይት ሊያደርግ ነው።

በክለቡ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በመቅረብ በክለቡ በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ሰፊ መብራሪያ የሰጡት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በርካታ ነጥቦችን በዝርዝር ያነሱ ሲሆን በዋናነት የክለቡ ከፍተኛ ወጪ በሆነው ከተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ሳምንት ከቡድኑ አባላት ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸውን ተናግረዋል።

“ከተጫዋቾቻችን ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ውይይት እናደርጋለን። ደሞዛቸውን በቀጣይ ሳምንት ገቢ እናደርጋለን። ገቢ ካደረግንላቸው በኃላ ግን ከተጫዋቾቻችን ጋር ውይይት እናደርጋለን። ምክንያቱም አብዛኛው ወጪያችን (ከፍተኛ ወጪያችን) የያዘው የተጫዋቾች ደሞዝ ነው። ይህንን ወጪ እንዴት መጋራት እንችላለን በሚል ውይይት በማድረግ እነርሱም ሳይጎዱ ክለቡም ሳይጎዳ ተጋግዘን ቀጣይ ውድድር ዓመት በሚኖርበት ሰዓት የተሻለ ነገር መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ዙርያ ውይይት እናደርጋለን።” ብለዋል።

የውድድሩ መቋረጥ በክለቡ ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ እና በዚህም ምክንያት የሚያገኛቸው የገቢ ምንጮች እየደረቁበት መሆኑን አስመልክቶ የተናገሩትን ሀሳብ በቀጣይ ፁሑፋችን ይዘን የምንመለስ ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ