የ1996 የፕሪምየር ሊግ ድል ትውስታ – በወቅቱ ኮከብ ተጫዋች ሙሉጌታ ምህረት

በዛሬው የትውስታ አምዳችን ሀዋሳ ከተማን 1996 ላይ በአምበልነት እየመራ ከክለቡ ጋር ቻምፒዮን የሆነውን እና በግሉ የሊጉ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን ያሳካው ሙሉጌታ ምህረትን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

ትውልዱ የበርካታ ተጫዋቾች መፍለቂያ ከሆነው የሀዋሳው ኮረም ሠፈር ፤ ከእግር ኳስ ጋር የተዋወቀውም በኮረም ሜዳ ነበር። በፕሮጀክት የታዳጊነት ጊዜውን ካሳለፈ በኃላ በተክለ ሰውነቱ እና የጨዋታ ስልቱ ከታዳጊ ወጣት የፕሮጀክት ቡድን በቀጥታ 1992 ላይ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ ሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን በመግባት ከሊጉ ጋር ተዋወቀ። በቡድኑ ውስጥ የነበረው ፈጣን ዕድገት የተነሳ በፍጥነት እየጎላ መጥቶ የክለቡ ቁልፍ ተጫዋች ከመሆን አንስቶ የአምበልነት ኃላፊነትን እስከመረከብ ደርሷል። በ1996 ሀዋሳ ከተማ በአሰልጣኝ ከማል አህመድ እየተመራ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የሳመ የመጀመሪያ የክልል ክለብ ሲሆን ቡድኑን በተከላካይ አማካይነት እንዲሁም በአምበልነት በመምራት ሙሉጌታ ምህረት የታሪኩ አካል ነበር ።

በሀዋሳ ከተማ የጀመረው የእግር ኳስ ስኬቱ 1998 ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ በጥብቅ እንዲፈለግ መነሻ ሆኖት ወደ ፈረሰኞቹ ቤት አምርቶ ሁለት ዓመታትን በክለቡ አሳልፏል፤ ሁለተኛ የሊግ ክብሩንም አሳክቷል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል በሚሊኒየሙ ዳግም ወደ አሳዳጊ ክለቡ ሀዋሳ ከተማ በመመለስ የሁለት ዓመታትን ቆይታ አድርጎ 2002 ላይ ደግሞ ደደቢትን በመቀላቀል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ተጫውቷል። በወቅቱ በደደቢት በቁልፍ ተጫዋችነቱ የቀጠለው ሙሉጌታ 2004 ላይ በድጋሚ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢፈለግም ትዳር መመስረት ዕቅዱ ስለነበር ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ልጅነት ክለቡ በመመለስ ጫማውን በይፋ በተዘጋጀ ልዩ የሽኝት ፕሮግራም እስከሰቀለበት 2008 ክረምት ድረስ ቆይቷል።

ለአስራ ሰባት ዓመታት እግር ኳስን የተጫወተው እና በብዙዎች ዘንድም በፀባዩ “አመለ ሸጋ” የሚል ስም ያገኘው ሙሉጌታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመጫወት በአምበልነት በመምራትም ያሳለፈ ሲሆን የሴካፋ ዋንጫንም ከሀገሩ ጋር አሳክቷል፡፡ የቀድሞው ተወዳጅ አማካይ በትውስታ አምዳችን የግል እና የክለብ ስኬትን ስላጣጣመበት የ1996ቱ የውድድር ዓመት እንዲህ ያወሳል…

“1996 እንደሚታወቀው ሁሉም የሀዋሳ እና የአካባቢው ህዝብ የተደሰተበት ጊዜ ነበር ፤ እጅግ በጣም መልካም ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ለኛ በሀዋሳ እግር ኳስ ውስጥ ላለነው ተጫዋቾች እና ለኮቺንግ ስታፉ ጭምር የነበረው ስሜት የተለየ ነበር። ከዚያ ብሎ በ1992 እና 93 ሀዋሳ ከተማ ጠንካራ ተጫዋቾቹን እነ ዘውዱ በቀለ ፣ ሰብስቤ ደፋር ፣ ገረሱ ሸመና እና አፈወርቅ ዮሐንስን አጥቶ ነበር። ለቀጣዩቹ ሁለት ዓመታትም ላለመውረድ ነበር የሚጫወተው። ነብሱን ይማረው እና በአሰልጣኛችን ታመነ ይርዳው ስር ብዙ ወጣት ተጫዋቾች ወደ ክለቡ መጥተው ጥሩ ቡድን ተሰርቶ ነበር፤ ሆኖም አጋጣሚ እሱም በሞት ተለየን። ከዚያ ነበር ጋሽ ከማል የመጡት፤ የወቅቱ ቁልፉ ሰውም እሳቸው ነበሩ።

” በወቅቱ ወጣቶች ስለነበርን ሁለቱን ዓመታት ላለመውረድ ተጫወትን፤ ሆኖም አንድ ላይ ነው የቆየነው። ትልልቅ ተጫዋቾች እንደ እነዮሴፍ ተስፋዬ ፣ ዘላለም አልጣህ ፣ ፀጋዬ ዜና፣ ጥላሁን እና ሰለሞን ከበደ (ሽማሙ)ን የመሳሰሉ በቡድኑ ውስጥ ነበሩ። ከነሱ ጋር ተዋህደን 1996 ላይ ጠንካራ መሆን ቻልን። በወቅቱ ሀዋሳ ከነማ በሜዳው የማይደፈር ከሜዳው ውጪም ጠንካራ ነበር። እኔ በግሌም ጥሩ ተጫዋች የሆንኩበትም ዓመት ነበር፡፡ በእርግጥ በወቅቱ እነዮሴፍ እና ዘላለም ለኛ ጥሩ ልምድ ይሰጡን ነበር ፤ ለኔም ለበኃይሉ ደመቀም በአጠቃላይ ለነበሩት በሙሉ። እና ያ ዓመት ለሁላችንም አሪፍ ነበር ፤ በተለይ ለኔ የተሻለ ነበር። የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ከመሆናችን ባሻገር እኔ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋችም ነበርኩ። ለኔ ጥሩ የጅማሬ ጊዜም ነበር። እንደ ቡድንም በጣም ድንቅ ነበርን። የኛ አልሸነፍ ባይነት እና ጥንካሬ ሀዋሳ ላይ ደግሞ የደጋፊው ስሜት ሁሉም ነገር በጣም አሪፍ ነበር። ካለፉት ላለመውረድ ከተጫወትንበት ጊዜም አንፃር በጣም አሪፍ ጊዜ ነበር ብዬ ነው የማስበው።

“እኔ ልረሳሁ የማልችለው በዛን ጊዜ አዕምሮዬ ውስጥ የሚመላለሰው ላለመሸነፍ የምናደርገው ትግል ነው፤ በተለይ ከሜዳችን ውጪ። ምንም የተለየ ነገር የለም ብለን እናምን ነበር። እኛ ሲጀመር ለቻምፒዮንነት አልነበረም የተነሳነው፤ በብዛት ወጣቶች ስለነበርን፡፡ ሁለት ዓመት ላለመውረድ የተጫወተ ቡድን ቻምፒዮን ይሆናል ብሎ ማንም የገመተ ሰው አልነበረም። ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቆየን ስንመጣ መሀል ላይ እየተጫወትን በምንሄድበት ወቅት ማሸነፍ ስንጀምር ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ርቆን ሄዶ ነጥብ እየጣለ ሲመጣ ለኛ ተመቸን። አጋጣሚ ሆኖ ለዛ ደረስን እንጂ ማንም አልገመተውም። ግን ከዛ በኃላ ከውጤቱ ተነስተን ሁሉም ተጫዋች ላለመሸነፍ የሚያደርገውን ትግል ጨመረ ፤ በሄድበት ቦታ ሁሉ። በተለይ ከሜዳ ውጪ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፤ ብዙ ፍፈተናዎች አሉት። ሁሉም ያን ተቋቁሞ ያለውን በሙሉ እየሰጠ በሞራል ነበር ስንጫወት የነበረው። ያ ቡድን ከአዕምሮዬ አይጠፋም፤ ሁሉም ቦታ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ደግሞ በጣም ጥሩዎች ነበሩ። ጠንካሮች እና በዲሲፕሊንም በሁሉም ነገር የተሟሉ ነበሩ።

“ያኔ ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት የነበረው ስሜት ከባድ ነበር። እኛ አሰላ ላይ ከሙገር ነበረን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ ነበር የተለያየው። አጋጣሚ ሆኖ በሰዓቱ ፕሪምየር ሊጉ ለአስራ አምስት ቀን ተቋረጠ። ከዚያ ጨዋታችንን በሜዳችን ነበር የምናደርገው። ቻምፒዮን ለመሆን በሁላችንም ውስጥ ጉጉቱ ነበር። ቀኑ ደግሞ በተራዘመ ቁጥር ተፅዕኖው ከባድ ነበር። ሆኖም የመሸነፍ ስሜት ውስጣችን የለም። እግር ኳስ ስለሆነ ያቺ ቀን እና ሰዓት እስክታልፍ ድረስ በጣም ጉጉት ነበር። ቢሆንም ያ ሁሉ አልፎ የጨዋታው ዕለት ደረሰ ኒያላንም 3-1 አሸንፈን ዋንጫውን አንስተናል።

“ከጨዋታው በኃላ በጣም የሚገርም ስሜት ነበር የተሰማን። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ ክልል ወጥቶ አያውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ በእኛ በመሆኑ እጅግ በጣም ደስ ብሎናል። ከዚያ ቀደም ደቡብ ውስጥ ክለቦች ራሱ የሉም ነበር ፤ ከአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ በቀር። አሁን ያሉት እነሲዳማ ፣ ድቻ ፣ ወልቂጤ ከዛ በኃላ የመጡ ናቸው። አጠቃላይ ህብረተሰቡም የአካባቢውም ህዝብ ህብረቱ እጅግ በጣም ደስ ይል ነበር። ስሜቱን ለመግለፅ እስከሚከብድ ድረስ ነው የተጨፈረው። በእግር ኳስ ህይወቴ እሱ ነው የኔ የመጀመሪያው ደስታዬ። ወደ ውጪ ወጥተን ሁሉ አናውቅም ነበር፤ የዛን ሳምንት በደስታ ውጪ ነበር የምናሳልፈው፤ ለሊት ነበር የምንገባው እና ደስ ይል ነበር። ሁሉም ለፍቶ ስለሆነ በቃ ከህዝቡ ጋር ይደሰት ነበር፤ የለፋበትን ሁሉም እየተዝናና እየተጫወተ ነበር። ሁሉም ተጫዋቾች ጥሩ ጊዜ ነበራቸው፤ አንድ ላይ ጊዜውን አሳልፈዋል፡፡ ደስ የሚለው ደግሞ ሁሉም ህብረተሰብ የተካፈለበት መሆኑ ነው “፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ