ያለፉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ተጫዋች…

ሶከር ኢትዮጵያ ከአንባቢዎቿ እና ከአርታኢዎቿ በሰበሰበችው ድምፅ መሰረት ያለፉት አምስት ዓመታት የሊጉ ምርጥ ተጨዋች ታውቋል።

የሃገር ውስጥ እግርኳስ ላይ ትኩረቷን አድርጋ የምትሰራው ሶከር ኢትዮጵያ ባሳለፍነው አርብ ለአንባቢዎቿ እና ለአርታኢዎቿ ያለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ተጨዋችን ማን እንደሆነ እንዲመርጡ እድል ማመቻቸቷ ይታወሳል። ከዓርብ አመሻሽ እስከ እሁድ ቀጥር ድረስ በተሰበሰበ የ1ኛ ዙር ድምፅ መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ አስቻለው ታመነ ከተሰጡት ድምፆች 56.5%፣ የሲዳማ ቡና የመስመር አጥቂ አዲስ ግዳይ 23.1% እንዲሁም የመቐለ 70 እንድርታው አጥቂ አማኑኤል ገብረሚካኤል 20.4% በማግኘት ወደ መጨረሻ ዙር ምርጫ አልፈዋል። በመቀጠልም ወደ ሁለተኛና የመጨረሻ ዙር ምርጫ ያለፉት 3ቱ ተጨዋቾች ከእሁድ አመሻሽ ጀምሮ እስከ ዛሬ ረፋድ (4ሰዓት) ድረስ ድምፅ ሲሰጣቸው ቆይቶ ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው የሊጉ ያለፉት የአምስት ዓመታት ምርጥ ተጨዋች ተለይቷል።

በዚህም መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የኋላ መስመር ደጀን የሆነው አስቻለው ታመነ ከፍተኛ የአንባቢያን እና የአርታኢያን ድምፅ በማግኘት የሊጉ ያለፉት አምስት ዓመታት ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተመርጧል።

የሶከር ኢትዮጵያ አርታኢዎች በሰጡት ድምፅ መሰረት አስቻለው ታመነ አዲስ ግዳይ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን በማስከተል ያለፉት አምስት አመታት ምርጥ በመባል ተመርጧል። አንባቢያን በሰጡት አጠቃላይ 1042 ድምፅ ደግሞ አስቻለው 520 (50%) ድምፅ በማግኘት ኮከብ ተብሎ ተመርጧል። አማኑኤል በበኩሉ 382 (37%) ድምፅ በማግኘት 140 (13%) ድምፅ ያገኘውን አዲስ ግዳይ በመብለጥ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በጠቅላላው በተሰበሰበው ድምፅ ስሌት መሰረት አስቻለው ታመነ የላቀ ቁጥር በማስመዝገብ አማኑኤል እና አዲስን በማስከተል የሊጉ ያለፉት አምስት ዓመታት ምርጥ ተብሎ ተለይቷል።

በዲላ ከተማ ውልደት እና እድገቱን ያደረገው አስቻለው በ2008 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመምጣቱ በፊት በደደቢት እና ዲላ ከተማ ግልጋሎት ሰጥቷል። በከፍተኛ እድገት ላይ የሚገኘው ይህ ቀልጣፋ ተከላካይ ከ2007 ጀምሮ በክለብ እና በብሄራዊ ብድን ደረጃ ጥሩ ስኬትን አጣጥሟል። በተለይ ይህ ግዙፍ ተከላካይ ካለፉት አምስት አመታት በሁለቱ (2008 እና 2009) ከክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መልካም የውድድር ጊዜን በማሳለፍ የሊጉ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ መመረጥ ችሏል። በብሄራዊ ብድን ደረጃም ተጨዋቹ ከ2007 ጀምሮ በወጥነት ሀገሩን ሲያገለግል ቆይቷል።

ምርጫውን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ከአስቻለው ጋር ያደረገችውን አጭር ቆይታ ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ