“ምርጥ መባሌ ይገባኛል” አስቻለው ታመነ

ያለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ በሶከር ኢትዮጵያ አንባቢያን እና አርታኢያን የተመረጠው አስቻለው ታመነ ስለምርጫውና ስላሳለፋቸው አምስት ዓመታት ሃሳቡን በአጭሩ ሰጥቶናል።

ያለፉት አምስት ዓመታትን እንዴት ትገልፃቸዋለህ?

“ያለፉት 5 ዓመታት በጣም ጥሩ ነበሩ። ደደቢት ከነበርኩበት 2007 ዓ/ም ጀምሮ ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ። በተለይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በግልም ሆነ በቡድን መልካም ጊዜ ነበረኝ። በብሄራዊ ብድን ደረጃም ከ2007 ዓ/ም ጀምሮ በቋሚነት ግልጋሎት ስሰጥ ቀይቻለሁ።”

እድገትህ ፈጣን ነበር ማለት ይቻላል….?

“ልክ ነው። እድገቴ በጣም ፈጥኗል። ነገር ግን እድገቴን ያፋጠንኩት በግሌ በማደርጋቸው ነገሮች ነው። እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፈጣሪ እርዳታ በመቀጠል በግሌ በጣም ለፍቻለሁ። ከቡድን ልምምድ በተጨማሪ በግሌ ልምምዶችን እሰራ ነበር። ይህ ደግሞ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በቶሎ እንድደምቅ አድርጎኛል።”

ያለፉት አምስት ዓመታት ምርጥ መባል ይገባኛል ትላለህ?

“እንደገለፅኩት ወደ ሊጉ ከመጣሁ ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ። ባለፉት አምስት ዓመታትም ጥሩ እንደነበርኩ ይሰማኛል። በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እንኳን ከ2007 ጀምሮ የተደረገ አንድም ጨዋታ አላለፈኝም። ወደ ብሄራዊ ቡድኑ የሚመጡ ሁሉም አሰልጣኞች በቋሚነት ሲመርጡኝ ነበር። በክለብም ያለው ነገር ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ብቃቴ እኔ ባልኩት ብቻ ሳይሆን ህዝብም የሚፈርደው ነው። ምክንያቱም እግርኳስ በአደባባይ የሚታይ ስለሆነ ሁሉም ነገር ግልፅ ነው። በግሌ የስፖርት ቤተሰቡ የመረጠው ምርጫ ልክ ነው ብዬ አስባለው። ስለዚህ ምርጥ መባሌ ይገባኛል። ይህንን ስል ግን የተፎካከሩኝ ተጨዋቾች ጥሩ አልነበሩም እያልኩ አደለም። አማኑኤልም ሆነ አዲስ ጥሩ ጊዜ አሳልፈዋል። ነገር ግን በግሌ የተሻለ ነገር ያለኝ እኔ ነኝ ብዬ አስባለሁ።”

በእቅድህ መሰረት ነው ያለፉትን አምስት ዓመታት ያሳለፍከው?

“እውነት ለመናገር ከዚህ የተሻሉ እቅዶች ነበሩኝ። በጠቅላላ ያሰብኩትን ነገር ሁሉ በአምስቱ ዓመታት አሳክቻለው ብዬ አልዋሽክም። ክፍተቶች ነበሩ። በዋናነት ከኢትዮጵያ ውጪ የመጫወት አላማ ነበረኝ። ነገር ግን በራሴ ድክመት እና በጥቃቅን ነገሮች ይህንን ግቤን ሳላሳካ ቀርቻለሁ። ከዚህ ውጪ ግን ያሰብኩትን እንዳደረኩ ይሰማኛል።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ