ስለ ስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

አጭር በነበረው የእግርኳስ ህይወቱ ከዘጠናዎቹ መጀመርያ አንስቶ በኢትዮጵያ እግርኳስ ስማቸው ቀድሞ ከሚነሱ ከዋክብት አጥቂዎች መካከል አንዱ የነበረው ስንታየው ጌታቸው (ቆጬ) ማነው?

ለጎረቤት ቡና ጠጡ የሚል መልዕክት ለማድረስ ሲላክ ሁሉ ከእጁ የጨረቅ ኳስ የማይለየው፣ ከፍተኛ የእግርኳስ ፍቅር እንደነበረው የሚነገርለት ስንታየሁ ቆጬ ተወልዶ ያደገው በአርባምንጭ ከተማ 03 ቀበሌ ነው። በሠፈር በጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በአስራ ሁለት ዓመቱ ለትምህርት ቤት ውድድር አጠቃላይ ተመርጦ ወደ ፈረንሳይ ሀገር በመሄድ ለመጫወት ችሎ ነበር። የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ እጅግ አስደናቂ እንደነበር የሚነገርለት ቆጬ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለአየር መንገድ ሲ ቡድን ለሙከራ መጥቶ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ጎል ቢያስቆጥርም “ገና ህፃን ነው፣ በቁመቱ አጭር፣ አካሉም ብዙም ያልፈረጠመ ቀጫጫ ነው።” በሚል ሳይመርጡት የቀረበት አጋጣሚ አስገራሚ ነበር።

በመቀጠል መድን ቢ ቡድንም ሙከራ አድርጎ ቢቀበሉትም ከአርባምንጭ መጥቶ አዲስ አበባ ለመኖር የክፍያው መጠን ያን ያህል አጥጋቢ ባለመሆኑ ወደ አርባምንጭ ለመመለስ ችሏል። ከእነዚህ ሁለት ክለቦች የሙከራ ቆይታ በፊት ለሦስት ወራት ያህል ለሀዋሳ ከተማ ተጫውቶ እንደነበረ ይታወቃል። በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ድንቅ ተጫዋቾችን እንዳፈራ ከሚነገርለት አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ የተጫወተው ስንታየሁ ለደቡብ ሕዝቦች ምርጥ ተመርጦ ደሴ ከተማ ላይ በተካሄደው ውድድር ባሳየው አስገራሚ እንቅስቃሴ የእግርኳስ ህይወቱ መስመር የያዘበት አጋጣሚ ተፈጥሮለት በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ምርጫ ጉምሩክ ሊገባ ችሏል።

በወቅቱ ስንታየው ደሴ ላይ ያደረገውን ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከቱ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ነግረውናል። “ስንታየው ፈጣን፣ በጣም ጠንካራ የሆነ፣ ኳስ የሚቀበል፣ ሰው የመቀነስ አቅሙ ከፍተኛ የሆነ፣ በተገቢው ቦታ ተገኝቶ ተገቢ የሆነ ውሳኔ በመወሰን የአጨራረስ አቅሙ ጥሩ የሚባል፣ የሰውነት ጥንካሬ (ጡንቻው) አስገራሚ የሆነ ለዚህም ማሳያው በሚገርም ሁኔታ ከቁመቱ በላይ ዘሎ የግንባር ጎል የሚያስቆጥር ሁሉን አሟልቶ የያዘ ጎበዝ አጥቂ ነው”። በማለት ነግረውናል።

ስንታየሁ በጉምሩክ በተጫወተበት ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ከማጠናቀቁ በተጨማሪ ዋንጫም ማንሳት ችሏል። በ1990 ቅዱስ ጊዮርጊስን በመቀላቀል ለአምስት ዓመታት እጅግ የተሳካ በድል ያሸበረቁ ዓመታትን አሳልፏል። በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1990 በከፍተኛ ዲቪዚዮን ተሳትፎው አስደናቂ ጉዞ በማድረግ ድሬዳዋ ላይ በተደረገ የክልል ሻምፒዮና ድል አድርጎ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ባደረገው ብርቱ ትግል ውስጥ በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሊጉ እንዲመለስ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሦስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ቆጬ በግሉ የ1992 የውድድር ዘመን 15 ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ተሸልሟል። ከአሸናፊ ሲሳይ ጋር የነበራቸው አስደናቂ ጥምረትም በሊጉ ከታዩ አስፈሪ ጥምረቶች ግንባር ቀደሙ እና የማይዘነጋ ነበር።

ቁመቱ 1.64 ሜትር ብቻ በመሆኑ በቁመታቸው አጭር ከሆኑ አጥቂዎች ተርታ ቢመደብም ከረጃጅም ተከላካዮች በላይ በመዝለል በግባሩ ጎል ማስቆጠር ይችልበታል። ለዚህም ማሳየው በ1992 ቅዱስጊዮርጊስ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ከዮጋንዳው ኤስሲ ቪላን በአዲስ አበባ ስታዲየም 3-0 በረታበት ጨዋታ ቆጬ ካስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አንዱ ከተከላካዮች በላይ ዘሎ በግንባሩ ያስቆጠራት ጎል ትጠቀሳለች።

በየጨዋታው ጎል ካላስቆጠረ እንቅልፍ እንደማይተኛ የሚናገረው ቆጬ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት ችሏል። በተለይ በቦትስዋና በተካሄደው የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ ላይ አፀባራቂ የሆነ እንቅስቃሴ ማሳየቱ ብዙዎች የስፖርት ቤተሰቦች የማይዘነጉት እውነታ ነው። በእሱ ዘመን የተዋጣላቸው የሚባሉ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ለመግጠም የሚቸገሩት አጥቂ እንደሆነ የሚመሰክሩለት ቆጬ እንደ ነበረው ብቃት ብዙም በሜዳ ላይ ሳይታይ በሁሉም ዘንድ እንደተወደደ በ1995 እግርኳስን አቁሞ ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄዷል። የዚህ ድንቅ የዘጠናዎቹ ኮከብ አጥቂ ስላሳለፈው የእግርኳስ ህይወቱ እና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ ከረዥም ዓመታት በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

“ቃለ ምልልስ ለማድረግ ስለፈለጋችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ። ከምንም አስቀድሜ ግን ፈጣሪ የኢትዮጵያን ህዝብ ከኮሮና መቅፀፍት እንዲጠብቅ እመኛለሁ። ከአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ጀምሮ ዋንጫ አንስቻለሁ። እንደገናም ደግሞ ኮከብ ተጨዋችም ተብያለሁ። ደቡብ ህዝቦች ላይም ተመርጬ ጎሎችን አስቆጥር ነበር። ጉምሩክም ስመጣ ፊናንስ ላይ ዋንጫ አንስተናል። ጊዮርጊስም ቤት እያለሁ ብዙ ዋንጫ አግኝቻለሁ። በብሄራዊ ቡድንም ደረጃ ጋቦሮኒ ላይ ያደረግነው ነገር ጥሩ ነበር። በሴካፋም ላይም እንደዛው። በአጠቃላይ በሃገሬ ከተጫወትኩባቸው ጥቂት አመታት ውስጥ ብዙ ዋንጫዎችን እንደ ቡድንም እንደ ግልም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመባል አግኝቻለሁ። እነኚህ ስኬት ሊሆኑ ይችላሉ ለእኔ ግን ስኬት አልነበሩም። ምክንያቱም እኔ ዋነኛ ዓላማዬ እና ምኞቴ ከሃገር ውጪ መጫወት ነበር። ይህንን ስላላሳካሁ ስኬታማ ነኝ ብዬ መናገር ይከብደኛል። እርግጥ ይህንን እድል ከአንዴም አራት ጊዜ አግኝቼ ነበር። ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።

“በቅዱስ ጊዮርጊስ እያለሁ ጥሩ የሆነ ስኬት ነበረኝ። ልክ እኔ ጊዮርጊስ እንደገባው ቡድኑ ወርዶ ነበረ። ነገር ግን ወዲያው ነው ያደግው። እኔም ወዲያው ኮከብ ግን አግቢ ሆንኩ። እንደውም አስታውሳለሁ እኔ ወደ ክለቡ ስሄድ የክለቡ ታላላቅ ተጨዋቾች እነ ሙሉጌታ ከበደ፣ ፍሰሃ በጋሻው፣ አሸናፊ ሲሳይ እና ሌሎችም የነበሩበት ወቅት ነበር። እና ቋሚ ለመሆን እራሱ የሚከብድ ይመስል ነበር፣ ግን እኔ እንደገባሁ ነው ቋሚ የሆንኩት። ጎሎችንም በደንብ አስቆጥር ነበር። እንደውም በአንድ ዓመት ውስጥ ከ40 በላይ ጎሎችን አስቆጥሬ አቃለሁ። ጎል ሳላስቆጥር ከወጣሁ እንቅልፍ አልተኛም ነበር። ቡድኔ ጊዮርጊስም ያኔ አቻ መውጣትን በተዓምር የማይቀበልበት ጊዜ ነበር።

” በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በሁሉም እርከን ጥሩ ተጫውቻለው። በተለይ ለታዳጊዎች ብሄራዊ ቡድን ተመርጬ ቦትስዋና ጋቦሮኒ ላይ በተካሄደው ውድድር ጥሩ ነገር አድርገን ነው የተመለስነው። እንደውም ለዋንጫ ልናልፍ ብለን በዳኛው ተፈፀመብን ደባ ሳይሳካልን በግብፅ ተሸንፈን ቀርተናል። ግን የቦትስዋና ህዝብ እንኳን በውድድሩ ባሳየነው አቋም ተገርሞ የአፍሪካው ብራዚል ብሎን ነበር።

” አሁን ሆኜ ያለፈውን ጊዜ ዞሬ ሳየው ኢትዮጵያ ካላት አቅም መነሻነት የሚገባትን ቦታና ደረጃ አላገኘችም እላለሁ። በእኔ ጊዜ እንኳን ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ነበሩ። ከሃገር ውጪ የመጫወት እድሉ ሁላ ነበረን። ነገር ግን ሳይሆን ቀርቷል። እንደውም እኔ በጣም የሚቆጨኝ ነገር ከሃገር ውጪ መጫወት አለመቻሌ ነው። በአውሮፓ መድረክ መጫወት አለመቻሌ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ አለመድረሱ በጣም ያሳዝነኛል፣ ያሳስበኛል፣ ይቆጨኛል። እኔም ኳስን ሳልጠግብ ነው ከሃገር የወጣሁት። ከግብፅ ጋር በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ስንጫወት ዳኛ በመታሁበት እና በክለብ ደረጃ ከኬንያ ክለብ ጋር ስንጫወት ‘ከአቅም በታች ተጫውቷል’ በሚል በተቀጣሁበት ሁለት አጋጣሚዎች ብዙ ነገር ሳላደርግ ቀርቻለሁ።

” ቅፅል ስሜ ቆጬ የተባለው ልጅ እያለሁ ነው። 03 ቀበሌ አብሮኝ ኳስ የሚጫወት እና 1ኛ ክፍል የምንማር መኮንን የሚባል ጓደኛ ነበረኝ። እና አንድ ጊዜ ሰፈር ውስጥ ስንጫወት ሊቆጣጠረኝ አልቻለም። አንዴ እየጎተተ አንዴ እያቀፈ ሊያስቆመኝ ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም። ከዛ ተናዶ ቆጬ ብሎ ሰደበኝ። ከዛ በኋላ ሁሉም ቆጬ ማለት ጀመረ። የሚገርመው እኔ ያወኩት በኋላ ነው። ብዙ ሰው “ቆጬ” የሚባል 11 ቁጥር አለ እያለ ያወራ ነበር። በአጠቃላይ ተጨዋችን እያታለልኩ ስለማልፍ ይመስለኛል ቆጬ የተባልኩት። መኮንንም ሙልጭልጭ ለማለት እንደሆነ ቆጬ ያለኝ ነግሮኛል።

“በአውሮፓ እና ባለሁበት እንግሊዝ ሀገር ማሰልጠን የምችልበት ኮርስ ነው። ዓላማዬ እኔ ያላገኘሁትን ዕድል የሀገሬ ተጫዋቾች እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ምክንያቱም እኔ በአውሮፓ ደረጃ የመጫወት ህልምና ምኞቱ ነበረኝ ፤ ሆኖም አልተሳካልኝም። ነገር ግን ሀገሬ ያሉ ታዳጊዎች እንዲሁም ዋናው ፣ ወጣቱ እና ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና እንዲያገኝ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ተሳታፊ የሆነ ቡድን እንዲኖረን እፈልጋለው። የሀገራችን ህዝብ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል። የእኔም ከፍተኛ ምኞት ሀገሬን ለዓለም ዋንጫ ማብቃት ነው። ተስፋ አለኝ ከፈጣሪ ጋር እዚህ ደረጃ እንድንደርስ የምችለውን ነገር ሁሉ አደርጋለው። ሀገሬም ካሉ የቀድሞ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ጋር በመተባበር ይህን ማድረግ ነው ምኞቴ።

“አርባምንጭ ለኳስ የሚመች ቦታ ስለሆነ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችም ይወጡበት ነበር። አሁንም ሃገሩ በደንብ የተሰራበት አይመስለኝም። ሀገሬ ስመጣ ወደ አሰልጣኝነቱ መግባቴ አይቀርም እና ታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጌ እሰራለው። ከሀገሬ ከወጣው አስራ ስድስት ዓመት ሆኖኛል። ቤተሰብ መስርቼ የሦስት ሴት ልጆች አባት ነኝ። ሊሊ የምትባል ባለቤት አለችኝ፤ በኑሮዬ በጣም ደስተኛ ነኝ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ