“የዘመናችን ከዋክብት ገፅ” ከፍፁም ዓለሙ ጋር…

የባህር ዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ የዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ እንግዳ ነው።

በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ ዶልፊን ሰፈር በሚባል ቦታ ላይ የተወለደው ፍፁም እንደማንኛውም ታዳጊ እግርኳስን ከሰፈሩ ጀምሮ ተጫውቷል። በክለብ ደረጃም ለጥቁር አባይ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ እና ፋሲል ከነማ አሁን ከሚገኝበት ባህር ዳር ከተማ በፊት ግልጋሎት ሰጥቷል። ለብሄራዊ ቡድንም ለቻን ማጣሪያ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ አማካኝነት ተመርጦ ተጫውቷል። በተለይ ዓምና ተጫዋቹ ቡድኑ ፋሲል ከነማን የዋንጫ ተፎካካሪ አድርጎ ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። በዘንድሮ የውድድር ዘመን ደግሞ ከፋሲል ተካልኙ ባህር ዳር ከተማ መልካም የሚባል ጊዜን በማሳለፍ 9 ጎሎችን ከመረብ አገናኝቷል። ሶከር ኢትዮጵያም ለተጫዋቹ የተለያዩ አጫጭር አዝናኝ ጥያቄዎችን አቅርባ ምላሹን እንደሚከተለው ታቀርበዋለች።

ይህንን ወቅት እንዴት እያሳለፍክ ነው?

ብዙ ጊዜ ቤት ውስጥ ነው የማሳልፈው። ቤት ውስጥ ግን ዝም ብዬ ቁጭ አልልም። አንዳንድ ልምምዶችን እሰራለሁ። ከዚህ ውጪ ፊልሞችን እያየሁ። በተጨማሪም መጽሐፍትን እያነበብኩ ጊዜዬን አሳልፋለሁ።

መጽሐፍ ማንበብ ትወዳለህ?

አዎ። አልፎ አልፎ መጽሐፍ ማንበብ ያስደስተኛል። በተለይ የታሪክ መጽሐፍትን ማንበብ ይመቸኛል።

ስምህን ለምን ቀየርክ?

ከፍፁም በፊት ስሜ ኤፍሬም ነበር። ዓምና ነው ኤፍሬም የሚባለውን ስሜን ለውጬ ፍፁም መባል የጀመርኩት። ይህም የሆነው ደግሞ በእናቴ ምክንያት ነው። የቤታችን የመጨረሻ ልጅ ስለነበርኩ እናቴ ፍፁም ነበር የምትለኝ። ከልጅነት ጀምሮ እስካሁን ፍፁም እያለች ስለሆነ የምትጠራኝ እሷን ደስ እንዲላት ብዬ ነው መጠሪያ ስሜን ሙሉ ለሙሉ ፍፁም ያስባልኩት።

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን ምን ትሆን ነበር?

ኳስ ተጫዋች ባልሆን ኖሮ ብዙ ነገሮችን ልሞክር እንደምችል ይሰማኛል። በተለይ ያደኩበት ሰፈር ታክሲ ተራ ስለነበረ ሹፌር የምሆን ይመስለኛል። ከዚህ ውጪ በፊት ከጓደኞቼ ጋር ከብረታ ብረት እና ከእንጨት(ጣውላ) ጋር የተገናኙ ሥራዎችን እንሰራ ነበር። ምናልባት ከእዚህ መነሻነት ወደሁለቱ ሥራ ልገባ እችል ነበር።

ሹፌር ሆነህ ታክሲ ባታሽከረክርም የራስህን መኪና በመንዳትህ ትፅናናለህ…

(ፈገግ እያለ) እርግጥ አሁን መንጃ ፍቃድ አለኝ ግን መኪና አልፎ አልፎ ነው የማሽከረክረው። ታክሲ ተራ በማደጌ ሹፌር ልሆን እንደምችል አስብ ነበር ነገርግን አሁን ላይ መኪና መንዳት አይመቸኝም። እፈራለሁ።

ለምንድን ነው የምትፈራው?

ከአደጋ ጋር በተያያዘ መኪና መንዳት እፈራለሁ። ምንም እንኳን እኔ ላይ የከፋ የመኪና አደጋ አጋጥሞኝ ባያውቅም ብዙ የግጭት አደጋዎችን በአይኔ አይቻለሁ። አንዴም ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ እየተጫወትኩ በሰርቢስ እየተጓዝን ከጭነት መኪና ጋር ተጋጭተን ነበር። ግን አደጋው የከፋ አልነበረም። ከዚህ ጋር በተያያዘ መኪና መንዳት ምቾት አይሰጠኝም። ከምንም በላይ ደግሞ ኳስ ተጨዋች ስለሆንኩ ለእግሬ እና ለአካላቶቼ እሳሳለሁ (እየሳቀ)።

አማካይ ተጫዋች ብትሆንም በርካታ ጎሎችን ታስቆጥራለህ። ካስቆጠርካቸው ጎሎች የማትረሳው ግብ?

ልክ ነው አማካይ ብሆንም ብዙ ጎሎችን አስቆጥራለሁ። ነገር ግን ዘንድሮ መቐለ 70 እንድርታን በሜዳችን ስናሸንፍ ያስቆጠርኳት ግብ ልዩ ስሜት ትሰጠኛለች። በህይወቴ የማልረሳት ምርጥ ጎል ነው ያስቆጠርኩት።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚያስቸግርህ ተጨዋች አለ?

እንደ ቡድን ከሆነ ፋሲልም ሆነ ባህር ዳር እየተጫወትኩ አዲስ ግደይ በጣም ያስቸግረን ነበር። እርግጥ አዲስ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ቦታ ላይ አደለም የሚጫወተው ነገርግን በጣም ቡድን ረባሽ ተጨዋች ነው። በግሌ ግን ስለሚያስቸግረኝ ተጨዋች አስተውዬ አስቤ አላቅም።

በእግርኳሱ ውስጥ ካሉ ግለሰቦች ሚስጥረኛህ ማነው?

አምሳሉ ጥላሁን (ሳኛ) በጣም ምርጥ ጓደኛዬ ነው። በጣም ነው የምወደው። ከጓደኛም በላይ እንደ ወንድም ነው የማየው። ከአምሳሉ በተጨማሪ ከድር ሃይረዲን መልካም ጓደኛዬ ነው።

ትዳር መስርተሀል?

አዎ ትዳር መስርቻለሁ። የምወዳት ባለቤት አለችኝ። የአንድ ዓመት ወንድ ልጅም አለን።

በእግርኳስ ያዘንክበት አጋጣሚ አለ?

በጣም ያዘንኩበት የእግርኳስ አጋጣሚ የተከሰተው ዓምና ፋሲል እያለሁ ነው። በ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሃ ግብር የነበረን የሽሬ ጨዋታ በጣም አሳዝኖኛል። ያንን ጨዋታ ብናሸንፍ ዋንጫ እናነሳ ነበር። ነገርግን ይህ አልሆነም። በእለቱ በነበረውም ነገር በጣም ተበሳጭቻለሁ፣ ተናድጃለሁ፣ አዝኛለሁ።

የተደሰትክበትስ የእግርኳስ አጋጣሚ?

ይህም ክስተት ዓምና ፋሲል እያለሁ የተፈጠረ ነው። የደረጃ ልዩነቱን ለማጥበብ መቐለን በሜዳችን ገጥመን 1ለ0 ስናሸንፍ በጣም ተደስቼ ነበር።

ምግብ ላይ እንዴት ነህ? በጣም የምትወደው እና የምትጠላው ምግብ ምንድን ነው?

ስጋ በጣም እወዳለሁ። በስጋ አልደራደርም። ስጋም ባይኖር ግን እንጀራ በወጥ መመገብ እወዳለሁ። አትክልት ነክ ነገሮችን ግን በፍፁም አልወድም። ቃሪያ፣ ቲማቲም፣ ሠላጣ፣ ጎመን እና የመሳሰሉትን አትክልት ነክ ምግቦች በልቼ አላቅም።

ፍፁም የተለየ ባህሪ ወይንም ልማድ አለው?

እውነት ለመናገር የተለየ ባህሪ የለኝም። ነገርግን ቀልድ ይመቸኛል። እንደ ጀማል ጣሰው አይነት ሰው ያዝናናኛል። የተለየ ባህሪ ከተባለ መሳቅና መጫወት መውደዴ ነው። ሰፈር ውስጥም ከሰፈር ልጆች ጋር ስንቀላለድ እና ስንፎጋገር ጊዜ እናሳልፋለን። ከዚህ ውጪ የወጣ ባህሪ የለኝም።

ቀልደኛ ነክ እንዴ አንተ?

እኔ እንኳን ቀልደኛ አደለሁም። ግን መፎጋገር እና መተራረብ እወዳለሁ። ጨዋታ እስከሆነ ድረስ መፎጋገር ያስደስተኛል። ሰፈር ውስጥም ብዙ ጊዜ ይተርቡኛል እንጂ እኔ ብዙም አልቀልድባቸውም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ