የሊግ ኩባንያው አዲስ ውሳኔ አስተላለፈ

ትናንት ስብሰባ ያደረገው የፕሪምየር ሊግ ኩባንያው ለወጣት ተጫዋቾች የሚበጅ ውሳኔ አስተላለፈ።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ክለቦች ውስጥ በቢጫ መታወቂያ (ቴሴራ) ተይዘው የሚገኙ አብዛኛዎቹ ታዳጊ ተጫዋቾች ለዘመናት የመጫወት እድል ሳያገኙ መቆየታቸው ይታወቃል። ክለቦችም “ለመያዝ ብቻ” ተጫዋቾቹን በተስፋ ቡድኖቻቸው አካተው በመያዝ የተስፈኞቹን ተስፋ ሲያጨልሙ ቆይተዋል። እርግጥ ክለቦች ከሚይዙት 25 ተጫዋቾች ውስጥ 5ቱ ከተስፋ ቡድን ያደጉ እንዲሆን ህግ ቢደነገግም ክለቦቹ ተጫዋቾቹን ለመጠቀም ሲያመነቱ ይታያል።

ይህን የተገነዘበው ሊጉ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን በአዲሱ ደንብ 5 ተጫዋቾች እንደከዚህ ቀደሙ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዋና ቡድን የሚያድጉ ሲሆን (ከ25 ተጫዋቾች መካከል ይሆናሉ) በአዲሱ ደንብ እነዚህ የሚያድጉ ተጫዋቾች ቢያንስ በቡድኑ 50 % ጨዋታዎች ላይ እንዲሳተፉ ግዴታ ተጥሏል። ሊጉ የውሳኔውን ተፈፃሚነት ከዳኞች በሚመጣ ሪፖርት መሠረት እንደሚቆጣጠርም ተገልጿል።  

የሊግ ኩባንያው ትናንት ባደረገው ስብሰባ ተጨማሪ አዲስ ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህም መሰረት ከተስፋ ቡድን በቢጫ ቴሴራ ለዋናው ቡድን እየተመላለሱ የሚጫወቱ የተጫዋቾች ቁጥር ከ5 ወደ 10 ከፍ እንዲል ሆኗል። ከዚህ ጋር በተያያዘ 25 የነበረው የቡድን አባላት ቁጥር ወደ 35 ከፍ ማለቱ ተጠቁሟል።
እነዚህ ውሳኔዎች ተስፋን አንግበው በየክለቦቹ ለሚገኙ የተስፋ ቡድን ተጫዋቾች ትልቅ ብሥራት ነው ተብሏል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ