የሴቶች የሊግ ውድድሮች የሚጀመሩበትን መንገድ አስመልክቶ ውይይት ተጠርቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና የ2 ዲቪዚዮን ውድድር የሚጀመርበትን መንገድ አስመልክቶ የመነሻ ሰነድ ለክለብ ተወካዮች ሊቀርብ ነው።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከሳምንታት በፊት በስሩ የሚገኙ የሊግ እርከናት ላይ የሚሳተፉ የወንዶች እና የሴቶች ቡድን አመራሮችን በካፍ የልህቀት ማኅከል ሰብስቦ ውድድሮች ሊጀመሩ የሚችሉባቸውን መንገዶች አስመልክቶ መነሻ ሰነድ ካቀረበ በኋላ ውይይቶችን ሲያወያይ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱም በውይይቱ ላይ የሴት ቡድን ተወካዮች ቢኖሩም እነሱን ያማከለ አቅጣጫ ሲቀመጥ አልተስተዋለም ነበር። ከስብሰባው በኋላም እነዚህ የሴቶች ቡድን ተወካዮች ለብቻቸው ተሰብስበው የራሳቸውን መንገድ ለመከተል ሲወያዩ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ፌዴሬሽኑ እንደሚደግፍ መግለፃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ከስብሰባው በኋላም ፌዴሬሽኑ በሴቶች ውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ አባላት ሴቶችን ያማከለ ጥናት አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ አድርጎ ነበር። ይህ የተዘጋጀው ጥናትም ተጠናቆ የፊታችን ሰኞ በካፍ የልህቀት ማኅከል ለኢትዮጵያ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡድን ተወካዮች እንደሚቀርብ ተሰምቷል። በውይይት መርሐ-ግብሩ ላይም በሁለቱ የሊግ እርከን ላይ የሚገኙ የቡድን ከፍተኛ አመራሮች እንዲገኙ ለክለቦች ደብዳቤ ተልኳል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ