ቢንያም ሀብታሙ የት ይገኛል?

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ቢንያም ሀብታሙ የት ይገኛል ?

የትውልድ እና እድገቱ ድሬዳዋ ከተማ ነው። የእግርኳስ ሕይወቱን በታዳጊ ደረጃ በድሬዳዋ ሲሚንቶ ጀምሮ ወደ ሙገር ሲሚንቶ በማቅናት ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ በሙገር የተሳካ ቆይታን ጨምሮ ለበርካታ የሀገራችን ክለቦች ተጫውቷል። ከሙገር ከለቀቀ በኋላ ለደደቢት፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ዳሽን ቢራ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ወልዲያ የተጫወተው ቢንያም ከ2000 እስከ 2006 በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማልያን ለብሶ የተጫወተ ሲሆን በ2010 በፋሲል ከነማ ካሳለፈ በኃላ ግን በትልቅ ደረጃ እየተጫወተ አይገኝም።

በ2010 መጨረሻ ከፋሲል ከነማ ጋር ከተለያየ በኃላ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በማምራት ጥሩ አጀማመር ቢያደርግም ጉዳት ስላጋጠመው ቀሪ የውል ጊዜውን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን አገልግሏል። የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመትን ከወልዲያ ጋር ያሳለፈው ይህ ተጫዋች ስለ ወቅታዊ ሁኔታው እና ከዋናው ሊግ የራቀበት ምክንያት አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ያደረገው ቆይታን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ከዋናው ሊግ የራቀበት ምክንያት

ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። በራስህ እና በሰዎች ችግር መነሻነት ብዙ ነገሮች ታጣለህ። በአንዳንድ ክለቦች ከባድ ወቅቶች አሳልፌያለሁ። ያለኝን ነገር አውጥቼ እንዳሳይ የሚያስችል በቂ ዕድል አልተሰጠኝም። በተለይም በ2009 በድሬዳዋ ከተማ የሕይወቴ ከባዱን ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ከሜዳ ውጭ የሚገጥሙኝ አንዳንድ ፈተናዎችም ነበሩ። የብቃት ችግር እንደሌለብኝ በደምብ አውቃለሁ። ግን ከራሴ ችግሮች ውጭ የነበሩት ነገሮች ናቸው ትልቅ ፈተናዎች የነበሩት።

ከዛ ውጭ ደግሞ ትንሽ የቤተሰብ ችግር ነበር። እናቴ ካረፈች በኋላ በጣም ከባድ ጊዜያቶች ነው ያሳለፍኩት፤ በእግርኳስ ሕይወቴ ላይም ትልቅ መሰናክል ነበር። ሌላው ጉዳትም አስቸግሮኝ ነበር። ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች ውጭም በግሌ አንዳንድ ችግሮች ነበሩብኝ፤ ትንሽ ቸልተኛ ነበርኩ። በአጠቃላይ በጣም ብዙ ፈተናዎች ነበሩ። እነሱን ግን እንደ ጥሩ ትምህርት ነው የምወስዳቸው።

አሁን ጊዜውን የሚያሳልፍበት ሁኔታ

ወቅቱ ኮሮና የተስፋፋበት ስለሆነ አብዛኛው ጊዜዬን ቤት ነው የማሳልፈው። ልጆች አሉ፤ ከነሱ ጋር አሳልፋለሁ። ከዛ ውጭም በግል ልምምዶች እስራለሁ። በዚ መልኩ ነው አብዛኛው ጊዜዬን የማሳልፈው።

ስለ ጥሩ ጊዜያቱ

ጥሩ ጊዜዬ የምለው ሙገር ሲሚንቶ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ዳሽን ቢራ ያሳለፍኳቸው ናቸው። ሙገር ሲሚንቶ ያደግኩበት ክለብ ነው፤ ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ። ከዛ በኃላ ደግሞ በሀዋሳ ከተማ እና ዳሽን ቢራ ጥሩ ጊዜያት አሳልፌያለው። በተለይም በሀዋሳ በሊጉ ከነበሩት ጥሩ ግብ ጠባቂዎች ተርታ ነበርኩ።

ስለ ብሔራዊ ቡድን ቆይታው

ብሔራዊ ቡድን ብዙ ጊዜ ተመርጫለው። ወደ ሰባት ስምንት የሚጠጉ ጨዋታዎችንም አድርግያለው፤ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። ያው ግብ ጠባቂ ስትሆንም ለስህተት ቅርብ ነህ አንዳንድ ስህተቶችም አይጠፋም። በእግር ኳስ ትልቁ ግብ ሃገርን መወከል ነው፤ ስሜቱም ልዩ ነው። ጓንቱን ስታጠልቅ ራሱ ይከብድሃል። ሀገርን መወከል እስከዛ ድረስ ነው ክብሩ።

የውጭ ግብ ጠባቂዎች በሊጉ ስለመብዛት

በሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎች እድገት ብዙ አሉታዊ ጎን አለው። ጥሩ ብቃት ሊኖራቸው ይችላል። ግን በክለቦች ውስጥ የሚስተናገዱበት መንገድ በጣም ይገርማል። የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂ በልጦ ጥሩ ብቃት ቢያሳይም፤ እነሱ በተደጋሚሚ ቢሳሳቱም የሚሰለፉት እነሱ ናቸው።

በቀጣይ ምን ታስባለህ?

በዚህ ወቅት ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። ከዚህ በፊት ትንሽ ቸልተኝነት ነበር። አሁን ግን ያንን ነገር ቀርፌ ቀጣይ የውድድር ዓመትን በጥሩ መንፈስ ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው። አቅም እንዳለኝ አውቃለሁ። ካለፉት ጊዜያትም ብዙ ትምህርት ወስጃለው።

በመጨረሻም በእግር ኳስ ሕይወቴ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሁሉንም ሰዎች ማመስገን እፈልጋለው። ቤተሰቦቼ ፣ ባለቤቴ እና በዙርያዬ የሚገኙትን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለው። ከዚህ በተጨማሪ በከባዱ ጊዜ ከጎኔ የነበሩት የጎሮ እና የሳብያን ሰፈር ጓደኞቼን በጣም አመሰግናለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!