መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፱) | አንድ ኮካ በመቶ ዶላር

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የታላቁን የእግርኳስ ሰው ዕድገት ፣ የእግር ኳስ አጀማመር ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ትውስታዎች እና የብሔራዊ ቡድን አስተዋፅኦን እያነሳንም ሰንብተናል። ዛሬ ደግሞ ከሜዳ ውጪ የተከሰተን አጋጣሚ እናነሳለን።


ማስታወሻ ፡
ለዚህ ፅሁፍ ግብዓት የሆነን በፋንታሁን ኃይሌ ፣ ኃይማኖት ቃኘው እና ተዘራ አለነ አማካኝነት ‘ይድረስ ለባነብረቱ’ በሚል ርዕስ የአስራ ሦስት ቀደምት ስፖርተኞች የሕይወት ታሪክ የተፃፈበት መፅሀፍ ነው።

በ1958 አምስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በቱኒዚያ አስተናጋጅነት ተዘጋጅቶ በጋና አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያም አምስተኛ ተሳትፎዋን አደረገች። ነገር ግን በሁለት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን አስተናግዳ በደካማ ውጤት ውድድሩን ለማጠናቀቅ ተገደደች። የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መንግሥቱ ወርቁም እንደለመደው ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችል ቀረ። ሆኖም ታላቁ የእግር ኳስ ሰው ለዚህ ውድድር ቱኒዚያ በነበረበት ወቅት ከሌሎች የቡድን ጓደኞቹ ጋር በአንድ መዝናኛ ቦታ ያጋጠመውን ነገር ልናካፍላችሁ ወደድን። ሁኔታው ፈገግታን ከመጫሩም ባሻገር የወቅቱን ተጫዋቾች ምንም እንኳን አማተር ቢሆኑም ስፖርታዊ ኃላፊነታቸውን የማይዘነጉ መሆናቸው የሚያሳይ ሲሆን ለሚያጠፉትም ጥፋት በዋዛ የሚያልፋቸው እንዳልነበርም ያስረዳናል።

መንግሥቱ ወርቁ ቱኒዚያ ላይ ከኢታሎ ፣ አዋድ እና ነፀረ ጋር ለመዝናናት ወጣ ብሎ ስለገጠማቸው ክስተት ይድረስ ለባንብረቱ በተሰኘው መፅሀፍ ላይ ተርኮታል።

“ቱኒዝያ በሄድንበት ጊዜ ታግተን የገጠመንን ላጫውትህ። ነፀረ ዳንስ ይወድ ነበርና አንድ ቦታ ሄደን ደንሰን እንምጣ ሲለን ከሆቴላችን ተደብቀን ወጣን፡፡ ኢታሎ ፣ አዋድ ፣ እኔና ነፀረ ሆነን ነበር የሄድነው። የሄድንበት ዳንስ ቤት በፈቃድ ተከፍቶ ለመንግሥት ቀረጥ ከመክፈሉ በስተቀር መዝናኛ ቤቱ ኃላፊነት አይወስድም። ብትከስም ‘ማን ሂድ አለህ ?’ የሚል መልስ ነበር የሚሰጥህ።

የሚታሰብልን በቀን ሦስት ዶላር ነበር፡፡ በአጠቃላይ የምትደርሰንን አሥር ዶላር እንደያዝን ዳንስ ቤቱ ገብተን ኮካ ኮላ አዘዝን፡፡ አልኮል አንጠጣም ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ ሕዝብ በሚያደንቅህና በሚጠብቅህ ሰዓት ሰክረህ ብትገኝ ያሳፍር ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ 0.05 ሳንቲም የሚከፍለን አልነበረም። የሕዝብና የሀገር ኃላፊነትና ፍቅር ብቻ ስላለን የትም እንሂድ የት ከአልባሌ ነገሮች ራሳችንን እንቆጥብ ነበር፡፡

ስንደንስ ቆየንና ነፀረን ‘አንተ ባሪያ በል በቃህ’ አልነው። ሳያስቸግረን ተስማማና ሒሳብ እንዲሠራልን ጠየቅን፡፡ የሒሳብ መጠየቂያው ቢል ሲመጣ 400 ዶላር ይላል። ነፀረ አየና ወደ እኔ አስተላለፈው እኔ ወደ እዋድ አዋድ ወደ ኢታሎ እንደ ኳስ ተቀባበልነው። እርስ በርስ መተያየት እና መፋጠጥ ሆነ። በዚያን ጊዜ ይህን መሰል ሁኔታ የሚዳፈር የአራዳ ልጅ ነፀረ ቢሆንም በሰዓቱ ግን ገንዘብ አልነበረውም። 

ኢታሎ ቀና ብሎ በሩን ሲመለከት ግድንግድ የዳንስ ቤቱ ጠባቂዎች ጥግ ይዘው ቆመዋል። ‘መንጌ ተመልከት !’ አለኝ፡፡ ምን ያካክላሉ መሰለህ? የኔ መናደድ መፍጨርጨር ምን ዋጋ አለው ፤ እንደ ዶሮ ጠምዘው ፣ ወገባችንን ሰባብረው ፣ አካላችንን ለያይተው ይጥሉናል ተባባልን፡፡ በኋላ በጣም አሳዘንናቸውና ወደ አረፍንበት ሆቴል ስልክ ደወሉልን፡፡ ጋሽ ይድነቃቸው ቱኒዝያዎች በሰጡት መኪና እየበረረ መጣ፡፡ በናይት ክለብ ውስጥ ሲያገኘን በጣም ተናደደ። ‘መንግሥቱ እና አዋድ ምን ነካችሁ ? እንዴት ትሳሳታላችሁ ?’ አለን፡፡ በመጨረሻ 4ዐዐ ዶላሩን ከኪሱ ከፍሎ ወጣን። ሒሳቡን ታዲያ በአራታችንም ስም መዝግቦ ይዞት ኢንተርናሽናል ውድድር ባደረግን ቁጥር ጋሽ ይድነቃቸው በክፍያ ወቅት ማስታወሻውን ነበር የሚያወጣው። ከሚሰጠን የኪስ ገንዘብ እየቆረጠ በየሄድንበት ሀገር ‘ይህን ያህል አለባችሁ ፤ በሉ ሃያ ሃያ ክፈሉ።’ ይለናል። ሌላ ዓመትም እንዲሁ እያደረገ ያወጣውን ገንዘብ ከአራታችንም እየቆረጠ አስመለሰ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!