ሶከር ታክቲክ | የአጨዋወት እቅድ ማዘጋጀት

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡         

ጸሃፊ – ማክስ ቤርማን
ትርጉም
– ደስታ ታደሰ

ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ተጋጣሚ ቡድንን በጥልቀት የመገምገም እና አያይዞም የጨዋታ እቅድ ማዘጋጀት በእግርኳሱ ዓለም የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ መደበኛ በሆኑት ታክቲካዊ መዋቅሮች ላይ መጠነኛ ለውጦች በማድረግ የሚዘጋጅ የጨዋታ እቅድ የማጥቃትና መከላከል መርሆችን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል የተሻለ የአጨዋወት ሥርዓት እንዲኖር እድል ይፈጥራል፡፡

በቀጣዩ ታክቲካዊ ትንተና የጨዋታ እቅድ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ዝርዝር ሃሳቦችን እንዲሁም ለእያንዳንዱ ተጋጣሚ ቡድን አጨዋወት የሚሆን የጨዋታ እቅድ በምን መልኩ ማርቀቅ እንደሚቻል እናጤናለን፡፡

የአጨዋወት እቅድ መዋቅራዊ ይዘት

አንድ የእግርኳስ ባለሙያ የሆነ ሰው የጨዋታ እቅድ ለማዘጋጀት አራቱን የጨዋታ ሒደቶች እንደ መነሻ ሊጠቀም ይችላል፡፡ አራቱ የጨዋታ ሒደቶች የሚባሉት፦ መከላከል፣ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግር፣ ማጥቃት እና ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረጉ ሽግግሮች ናቸው፡፡ በማስከተል እያንዳንዱን ተጋጣሚ ቡድን ያማከለ የጨዋታ ዕቅድ ምን ሊመስል እንደሚችል እናያለን፡፡ ለትንታኔ ያመቸን ዘንድ የጨዋታ ሒደቶቹን በተከታታይ አንቀጾች እየለያየን ብናቀርባቸውም ሁሉም የጨዋታ ሒደቶች የማይነጣጠሉ፣ አንዱ በአንዱ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ እንደሚያሳርፍ ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

                    የመከላከል ሒደት

ተጭኖ በመጫወት የተጋጣሚ ቡድንን የጨዋታ ምሥረታ መረበሽ

“ፕረሲንግ”ን ጥቅም ላይ የማዋል ዋነኛ ግብ የተጋጣሚ ቡድንን የጨዋታ ምሥረታ እንዲረበሽ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የተጋጣሚ ቡድንን የኳስ ምስረታ ይዘቶች በጥልቀት ለመተንተን ቀዳሚው ተግባር ይሆናል፡፡ በጨዋታ ወቅት በየትኛውም የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ አደራደር ልንተገብራቸው የምንችላቸው የተለያዩ ተጭኖ የመጫወት ዘዴዎች አሉ፡፡ “ፕሬሲንግ” በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ሊተገበር መቻሉን ልብ ልንል ይገባል፡፡ በባላጋራ የመከላከል ሲሶ በላይኛው የሜዳ ክፍል በተጋጣሚ ቡድን ላይ (Pressing High-Up The Pitch)፣ በሜዳው አጋማሽ ወይም መሃለኛው ክልል ላይ ተጋጣሚ ቡድንን የመጫን እንቅስቃሴ (Setting-Up Mid Block)፣ በጥልቀት ወደ ራስ የግብ ክልል ተጠግቶ  መከላከል (Low Block) በመባል የሚታወቁትን ታክቲካዊ ሃሳቦች መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከቅርፅ አንፃር ካየነው አንድ ቡድን በቀጠና የመከላካል ወይም ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የመከላከል ዘዴን ሊመርጥ ይችላል፡፡ በቀጠና የመከላከል ዘዴ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ነጻ ሆኖ ኳስ ሊያገኝ የሚችልበትን ቦታ እንዳያገኝ ማድረግ ላይ ያተኩራል፡፡ ለባላጋራ ቡድን ተጫዋች የመጫወቻ ክልልን በማጥበብ ጫና መፍጠር እንዲቻል ማድረግ ዋናው በቀጠና የመከላከል ዓላማ ነው፡፡ ተጫዋችን-በ-ተጫዋች መቆጣጠር ማለት ደግሞ በእያንዳንዱ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ላይ በቅርብ ርቀት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡ የባላጋራ ቡድን ባለው የአጨዋወት ዘይቤ እና በጨዋታ ምስረታ ላይ በሚያሳዩት የብቃት ደረጃ ተመስርቶ ሜዳ ላይ ለመተግበር የሚታለምን የ”ፕረሲንግ” ዓይነት መምረጥ ይቻላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የተጋጣሚ ቡድንን የጨዋታ ምስረታ መዋቅር ለይቶ ማወቅ ተጭኖ ለመጫወት የሚያስችለንን ተገቢ ፎርሜሽን  ለመምረጥ ያስችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ በሜዳው የላይኛው ክፍል “ፕረስ” በማድረግ የሚጫወቱ ቡድኖች የባላጋራ ቡድን የሚጠቀምበትን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ አደራደርን እንዲመስል ይሞክራሉ፡፡ ይህም በቀላሉ ተጫዋችን-በ-ተጫዋች ለመቆጣጠር እንዲችሉ ያግዛቸዋል፡፡

ከላይ በቀረበው ምስል ዩኒየን በርሊን የተባለው ቡድን 3-4-3 ፎርሜሽን በመጠቀም የሞንቼግላድባኽን ተመሳሳይ 3-4-3 ፎርሜሽን “ፕረስ” ሲያደርግ እናያለን፡፡ በዚህም ምክንያት ዩኒየኖች ተጫዋችን-በ-ተጫዋች በመቆጣጠር የሚደረገውን የመከላከል ዘዴ መተግበር ችለዋል፡፡

ቡድኖች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በጥልቀት አፈግፍገው ሲከላከሉ በኋለኛው መስመራቸው ላይ በተከላካይ ተጫዋቾች የቁጥር ብልጫ መውሰድ የሚያስችላቸውን ፎርሜሽን ይጠቀማሉ፡፡ እንደ ምሳሌ ለመውሰድ ያህል በሁለት አጥቂ ለሚጫወት ተጋጣሚ ቡድን ሦስት ተከላካዮችን መጠቀም የተለመደ ታክቲካዊ ዕቅድ ሆኗል፡፡ በእርግጥ ይህ ታክቲካዊ ቅድመ ዝግጅት የመሃል ተከላካዮች በተናጠል ኃላፊነት የ”1-ለ-1″ ፍልሚያ እንዳያደርጉ ይከለክላቸዋል፡፡

                  የኳስ ቁጥጥር ሒደት   

በጨዋታ ምስረታ ወቅት የተጋጣሚ ቡድንን “ፕሬሲንግ” ጥሶ መውጣት

የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማስቀጠል እና አመርቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመከወን በጥልቀት የታሰበበት እንዲሁም በጥንቃቄ ዝግጅት የተደረገበት የኳስ ምስረታ ሒደት ወሳኝ ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው ተጋጣሚ ቡድን ይህንን የጨዋታ ምስረታ አደረጃጀት ለመረበሽ ተጭኖ መጫወቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ተጋጣሚ ቡድን ለጨዋታው የትኛውን የ”ፕሬሲንግ” አጨዋወት ሊተገብር እንዳቀደም ከዚሁ እንቅስቃሴው መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ቀደም ሲል በቀረበው ምሳሌ ግላድባኾች የዩኒየን በርሊኖችን “ፕረሲንግ” ጥሶ ለመውጣት ይችሉ ዘንድ በኳስ ምስረታ ወቅት 3-5-2 ሲጠቀሙ እናያለን፡፡ ከታች በምስሉ እንደሚታየው የግላድባክ ተከላካዮች ሦስቱን የዩኒየን በርሊን አጥቂዎችን በተናጠል ከመቆጣጠራቸውም በላይ ሁለት የተከላካይ አማካዮች የያዘው የተጋጣሚ ቡድን የመሐል ክፍል ላይም የቁጥር ብልጫ ወስደዋል፡፡

ዩኒየን በርሊኖች የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ አደራደራቸው ላይ መጠነኛ ሽግሽጎችን በማድረግ ጫናዎችን ለመቋቋም እስከ እረፍት ሰዓት ድረስ  መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከኋላ መስርቶ በውጤታማነት ለመጫወት ታክቲካዊ ዕቅዶች ያላቸውን ፋይዳ ለማሳየት ይህ ድንቅ ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በ”ፕሮፌሽናል እግርኳስ” አውድ ሌላ አፅንኦት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ አንድ ቡድን ሁልጊዜም አማራጭ ዕቅድ ወይም “Plan B” ያስፈልገዋል፡፡ ተጋጣሚ ቡድን ከተገመተው የተለየ አሰላለፍ ይዞ ወደ ሜዳ ሊገባ ስለሚችል ቀድሞ ላልተጠበቁና ድንገታዊ  የፎርሜሽንን ለውጦች ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

የተጋጣሚ ቡድንን የመከላከል ድክመት መጠቀም 

የማጥቃት ሒደትን ፍሬያማ ለማድረግ አንደኛውና ዋነኛው ዓላማ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህም የተሻሉ የግብ አጋጣሚዎች ለመፍጠር ተጋጣሚ ቡድን በመከላከል አጨዋወቱ የሚታዩበትን ደካማ ጎኖች ማጤንና መለየት የግድ ይላል፡፡ የባላጋራው ቡድን ድክመት የተናጠል ተጫዋች ሆነ አጠቃላይ የመከላከል አደረጃጀቱ ዋናው ቁምነገር በጥሩ የማጥቃት ሒደት ይህን ደካማ ጎን በጥቅም ላይ ለማዋል መዘጋጀቱ ላይ ነው፡፡

የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል ድክመትን ለመጠቀም የተለመደው ዘዴ የመስመር ተከላካዮች ላይ ጫና በማሳደር ነው፡፡    በተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ ተወስዶባቸው ከቡድን አጋሮቻቸው እንዲነጠሉ በማድረግ ደካማውን የተከላካይ ክፍል ይበልጥ ማዳከም ይባላል፡፡ ዘዴው “Overload to Isolate” ታክቲክ ይባላል፡፡ በዚህ ዘዴ ኳሱ በአንደኛው የክንፍ መስመር በኩል ወደ ኳሱ አቅጣጫ በሚሮጡ ተጫዋቾች እንዲከበብ ይደረጋል፡፡ በዚሁ ቅጽበት በተቃራኒው መስመር ያለው የመስመር አማካይ ነጻ ስለሚሆን ለመቀባበያ አማራጭነት የሚጠቅም የጎንዮሽ ስፋት ያበጃል፡፡ በዚህ ምክንያት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ራቅ ያለውን የመስመር ተከላካይ ትተው ኳሱ ሊያመራ  ወደሚችልበት የመስመር አማካይ በመሄድ የ”1-ለ-1″ ፍልሚያ ለማድረግ ይዘጋጃሉ፡፡ የጨዋታውን ሒደት ፈጣን በሆነ ሁኔታ በመለዋወጥ ይህን የተረበሸ የተከላካይ አደረጃጀት መጠቀም ይቻላል፡፡ ከታች በቀረበው ምስል ሌቨርኩዘኖች በግራ መስመር በማጥቃት ሒደት ላይ ሲሆኑ የተጫዋቾች የ”1-ለ-1″ ግንኙነት የሚከሰቱባቸው ሁኔታዎችን ሲፈጥሩ እንመለከታለን፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁኔታዎች የሚፈጥሩት የቀኙ መስመር ላይ የቁጥር ብልጫ የሚያስገኝላቸውን ጫና በመጠቀም መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ይህ እኔግዲህ ፈረንጆቹ “Overload to Isolate” የሚሉት ታክቲካዊ ስትራቴጂ መሆኑ ነው፡፡

ከላይ በምስሉ ከታዩትና ለማጥቃት አመቺ ሁኔታዎችን ከሚፈጥሩት ሁኔታዎች ባሻገር የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል መዋቅራዊ ድክመትንም መጠቀም አንደኛው አማራጭ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ በአራት ተከላካዮች እና እንቅስቃሴያቸው መሃለኛው ክፍል ላይ የሚያመዝን አማካዮችን የያዘ ባላጋራ ቡድን ሲገጥም በመስመሮች ክፍተት ስለሚገኝ በዚሁ አቅጣጫ ማጥቃት የተሻለው አማራጭ ይሆናል፡፡ 


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡