​”በምንችለው አቅም ውጤቱን ለመቀልበስ እየሠራን ነው” ሱራፌል ዳኛቸው

በካፍ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታ የቱኒዚያው ሞናስቲርን ከሜዳ ውጪ ገጥሞ ሽንፈት ያስተናገደው ፋሲል ከነማ ውጤቱን ለመቀልበስ ባሉት ቀሪ ቀናት እየተዘጋጁ እንደሆነ ይታወቃል።

ዐፄዎቹ  ከወራት ዝግጀት በኋላ ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ ምንም እንኳን ሸንፈት አስተናግደው ቢመለሱም በነበራቸው ክፍተቶች መሻሻል ካደረጉ ውጤቱን መቀልበስ እንደሚችሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ተናግሯል።

የቱኒዚያው ጨዋታ ምን መልክ ነበረው?

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። በተለይ የመጀመርያው አርባ አምስት ደቂቃ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለናል። የተጫወትንበት ሜዳ በጣም አሪፍ ሜዳ ነው። ሆኖም ሜዳቸው ትንሽ አቅም ይፈልጋል። ምክንያቱም ታኬታ የመያዝ አቅም አለው። ሳሩ በጣም ስስ ስለሆነ እነርሱ የብሎን ታኬታ ነበር የሚጠቀሙት የብሎን ታኬታ ደግሞ ጠርዝ ስሌለው ስክት ብሎ ንቅል ነው የሚለው ይህ እነርሱን ጠቅሟቸዋል። እኛ ላይ ብዙ ተፅእኖ ያደረገብን ባይሆንም ትንሽ ግን ባት አካባቢ ስትሮጥ ያዝ በማድረጉ አቅም ይፈልግ ነበር። ይህንንም ተቋቁመን ጨዋታውን ተቆጣጥረን መውጣት ችለናል። ሆኖም በሆይ ሆይታ አዘናግተውን አንድ ጎል አስቆጥረዋል። በጣም በሚገርምህ ሁኔታ ዳኛውን ለማሳሳት እና እኛን ለመረበሽ ሳይነኩ ሜዳ ውስጥ በጣም ይጮሁ፣ ያዋክቡ ነበር። እኛም ወደ ራሳችን ተመልሰን ኳሱን ተቆጣጥረን እየተጫወትን ነበር። እነርሱ አጨዋወት የአየር ላይ ኳስ ወደ መስመር አሻግረው በቀጥታ ወደ ጎል ነበር የሚጥሉት በዚህ ነበር ጎሎች ያስቆጠሩብን ከዚህ ውጭ ተክቲካል ዲሲፒሊን በጣም ጥሩ ጎናቸው ነበር። በአጠቃላይ እኛም መጠቀም ሳንችል መቅረታችን እንጂ የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለን ነበር።

በሽንፈት ውስጥ በነበራችሁ ጥንካሬ ዙርያ ተጨማሪ ምን እየተሰራ ነው ?

እኛም እየሰራን ያለነው የነበረንን ጥንካሬ ይዘን ውጤቱን የምንቀለብስበትን መንገድ በማሰብ ነው። እነርሱ ምን ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉ አውቀናል። ተክለ ሰውነታቸው ይሄን ያህል ግዙፍ አይደለም። እንደ ሰሜን አፍሪካ ቡድኖች አይደሉም እርግጥ ነው ኳስ ይችላሉ። ታክቲካሊም ጥሩ ናቸው። እኛ ደግሞ በምንታወቅበት ኳሱን በሚገባ ይዘን በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ ከፈጣሪ ጋር ውጤቱን እንቀለብሳለን።

የቆሙ ኳሶች ዋጋ እንዳያስከፍሉ ምን ታስቧል? 

ትልቁ አቅማቸው ይሄ ነው። ጎሎችም የተቆጠሩብን በቆሙ ኳሶች በሚነሱ ነው። እኛ ደግሞ በተለይ ኳሱ ከመነሻው ወይም መንስኤውን ማስቀረት ላይ እየሰራን ነው። ኳሱ የሚነሳበትን ማቆም ከቻልን ኳሱን መስርተው መጫወት ስለማይችሉ መቆጣጠር እንችላለ። የሚገርምህ ሦስት ኳስ እንኳን ተቀባብለው አይደለም ጎል ያስቆጠሩብን። ስለዚህ እዚህም በመልሱ ጨዋታ በተመሳሳይ ሊያደርጉ ስለሚችሉ የአየር ላይ ኳሶችን አጨዋወት ስለሆነ ይን ከመነሻው ለመቆጣጠር እየሰራን ነው።

ውጤቱን ለመቀልበስ ተስፋ ስለማድረግ?

እንግዲህ እኛ እንጥራለን። አዲስ አበባ ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ጠንክረን እየሰራን ነው። በምንችለው አቅም ውጤቱን ለመቀልበስ ተረጋግተን ለመጫወት እናስባለን። ፈጣሪም ረድቶን ውጤቱን በሚገባ መቀልበስ ይቻላል ብዬ አስባለው።

© ሶከር ኢትዮጵያ