የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ሰበታ እና ድሬዳዋ ያለግብ ከተለያዩ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ይህንን ብለዋል።


አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለጨዋታው…

“በእኛ በኩል ከልምድ ማነስ እና ከትኩረት ማነስ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን መጨረስ ላይ ድክመት ነበረብን። ከዚህ በተረፈ ተከላካዮቻችን ላይ የእነሱን የመጨረሻ አጥቂዎችን መቆጣጠር ላይ ክፍተት ነበረብን። እሱን ለማስተካከል ጠንክረን እንሰራለን። በተረፈ ግን በጉዳት እና በሌሎች ምክንያቶች ያልተሰለፉ ተጫዋቾች ቡድኑን ጎድተውታል ማለት እችላለሁ። እንደጅምር እና ከነበረን የዝግጅት ጊዜ ማጠር አንፃር የተገኘው ውጤት ለእኔ ጥሩ እና አበረታች ነው።”

ስለግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል

“ደጋግሜ የምናገረው ነገር ነው። ለሀገራችን ግብ ጠባቂዎች ተገቢውን ሥልጠና ከሰጠናቸው እና ዕምነት ከጣልንባቸው የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ይችላሉ። ፋሲል አዲስ ነው ፤ ገና ወጣት ነው። ለእኔ ግን የጨዋታው ኮከብ እሱ ነበር ማለት እችላለሁ። ቁም ነገሩ ተገቢውን ሥልጠና እና ዕድል መስጠት ላይ ነው። ያ ከሆነ ጥቅሙ ለክለቡ ብቻ ሳይሆን የግብ ጠባቂ ችግር ላለባት ሀገራችንም ጭምር ነው።”

አሰልጣኝ ፍሰሐ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው…

“የወዳጅነት ጨዋታ ባለማድረጋችን እና በቶሎ ወደ አዲስ አበባ ባለመምጣታችን አየሩ ትንሽ እንደከበዳቸው ተጫዋቾቼ አሳውቀውኛል ፤ ቢሆንም ጥሩ ነው።”

ስለቡድኑ የአጨራረስ ችግር…

“የወዳጅነት ጨዋታ ባለማድረጋችን እነዚህን ነገሮች ማየት አልቻልንም። አንድ ጨዋታ ነው ከመከላከያ ጋር ያደረግነው ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ጨዋታ ነው የገባነው። ከመጣንም ሳምንት አይሆነንም። የአዲስ አበባ አየር ከባድ እንድሆነ ይታወቃል። ተጫዋቾቹ ታፍነዋል መጫወት አልቻሉም። ያገኘነውን አጋጣሚ አለመጠቀማችን ግን ዋጋ አስከፍሎናል።”

ስለሪችሞንድ ኦዶንጎ ጉዳት…

“የእሱ ጉዳት ከባድ ነው። ኢታሙናም ተጎድቶብን ተቀምጧል። ለጊዮርጊስ ጨዋታ ይደርሳል ብለን እናስባለን።”

ስለቀጣይ ጨዋታ ዝግጅት…

“ይሄ ጨዋታ ያለብንን ችግር አሳይቶኛል። ቀጣዩ ጨዋታ ከሦስት ቀን በኋላ ቢሆንም ባለችኝ ጊዜ ሰርቼ የተሻለ ነገር ለማምጣት እሞክራለሁ። ተመልሰን ለማሸነፍ ነው የምንመጣው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ