ሪፖርት | የመጋረጃ መግለጫው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ሰበታ ከተማን ከድሬዳዋ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

አዝናኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሰበታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የበላይነትን መውሰድ ቢችሉም ኳሶችን ወደ ሜዳው የላይኛው ክፍል በማሳደግ የጠሩ የግብ እድሎችን ግን መፍጠር አልቻሉም። ቡድኑ ያሉትን ተፈጥሮአዊ የፊት አጥቂዎችን በመጀመሪያ 11 ተመራጭ ውስጥ ያላካተቱት የአሰልጣኝ አብርሃሙ ሰበታ በ6ኛው ደቂቃ ያሬድ ሀሰን ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ ቡልቻ ሹራ ወደ ግብ ልኳት ኢላማዋን ሳትጠብቅ ከቀረችው ኳስ ውጭ ተጠቃሽ ሙከራን ማድረግ አልቻሉም።

በአንፃሩ ኳሱን የመቆጣጠር ፍላጎት ያልነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ከኤልያስ ማሞ እግር በሚነሱና የአጥቂውን ጁኒያስ ናንጂቡን አስደናቂ የመፈትለክ አቅምን በመጠቀም ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በዚህም ሂደት ናንጂቡ በ2ኛው ደቂቃ እንዲሁም በ16ኛው ደቂቃ ናንጂቡ በተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው ሪችሞንድ አቀብሎት የሞከራት እና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በግቡ ሙከራዎች ረገድ በአጋማሹ የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ27ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ በግል ጥረቱ ተጫዋቾችን አልፎ ሞክሯት ፋሲል ካዳነበት ኳስ በተጨማሪ በ36ኛው ደቂቃ መሳይ ጳውሎስ ኳስ በእጅ በመንካቱ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት ሳሙኤል ቢመታም ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው ወጣቱ ግብጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካኤል ሊያድንበት ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመሪያው በተሻለ ሙከራዎችን ያስመለከተ ነበር።

ሰበታ ከተማዎች በታደለ መንገሻ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እንዲሁም ተቀይሮ በገባው ፍፁም ገ/ማርያም አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የድሬዳዋው ግብጠባቂ ፍሬው ጌታሁን የሚቀመስ አልሆነም ፤ በአንፃሩ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በጁንያስ ናንጂቡ ላይ ብቻ የተጠለጠለ የማጥቃት ሂደትን ሲከተሉ የነበሩት ድሬዳዎች በሁለተኛው አጋማሽም በ61ኛው እና በ73ኛው ደቂቃ ናንጂቡ በግንባር እና ከግቡ ቅርብ ርቀት በእግሩ ጥሩ የማግባት አጋጣሚዎችን አምክኗል።

በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬያማ ሳይሆን ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ