ሪፖርት | ዐፄዎቹ ሊጉን በድል ጀምረዋል

የአዲስ አበባ ስታድየም ባስተናገደው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 አሸንፏል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ 2ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከግራ መስመር አሻግሮት በሙጂብ ቃሲም ተሞክሮ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከመስመር ላይ ባወጣው ኳስ ቀዳሚውን ከባድ ሙከራ አስተናግዷል። በከነዓን ማርክነህ እና አቤል ያለው ጥምረት ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት ጊዮርጊሶች ባልተለመደ መልኩ ደስታ ደሙን በአማካይነት መጠቀማቸው ትኩረትን ቢስብም በተሻለ መልኩ ኳስ ተቆጣጥረው ዕድል ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት በፋሲል ሳጥን ውስጥ ክፍተት ሊያስገኝላቸው አልቻለም። ፋሲሎችም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሱራፌል ዳኛቸው መሪነት በፈጣን ሽግግር በአመዛኙ ሽመክት በሚገኝበት በግራ መስመር በኩል ጥቃት ለመሰንዘር የሚያደርጉት ጥረት የግብ ዕድሎችን አላስገኘላቸውም።

17ኛው ደቂቃ ላይ በሱራፌል አማካይነት ከርቀት አደገኛ ሙከራ አድርገው በፓትሪክ ማታሲ የከሸፈባቸው ፋሲሎች ቀስ በቀስ ኳስ የዞ የመጫወቱን ተራ ወስደዋል። የተሻሉ የነበሩት ሙከራዎች ግን በ 24 እና 25ኛ ደቂቃዎች የፋሲሉ አምሳሉ ጥላሁን እና የጊዮርጊሱ ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ምት ሞክረዋቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁት ነበሩ። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ቀዝቅዝ ብሎ በታየው ጨዋታ ጊዮርጊሶች 29ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግዳይ ሳጥን ውስጥ ከከነዓን ተቀብሎ ባደረገው እና ሚካኤል ሳሜኬ ባዳነው ኳስ እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ በአቤል ያለው ከግራ መስመር ተመትቶ በግቡ አግዳሚ የተመለሰ ኳስ በሙከራ ተሽለው ታይተዋል። ሆኖም ጨዋታው ለዕረፍት ሊያመራ ጥቂት ሲቀረው ምንተስኖት አዳነ መሀል ሜዳ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ሱራፌል በቀጥታ ወደግብ የመታውን ኳስ ማታሲ በአግባቡ መያዝ ሳይችል ቀርቶ ሙጂብ ቃሲም ፋሲልን መሪ ያደረገች ኳስ ከመረብ አገናኝቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ይልቅ ቀዝቅዝ ያለ ነበር። በጨዋታው እንቅስቃሴ ጌታነህ ከበደን በአብዱልከሪም መሀመድ ቀይረው ያስገቡት ጊዮርጊሶች የተሻለ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ጌታነህ ወደ መሀል እየገባ የይሁን እንዳሻው እና ሀብታሙ ተከስተ ጠንካራ የመሀል ጥምረት ላይ የቁጥር ብልጫ ለማስገኘት እና ክፍተቶችን ለመፍጠር ቢሞክርም ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር ለፈረሰኞቹ ቀላል አልሆነም። 68ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሸጋገረው ደስታ ደሙ ያሻማው እና አዲስ በግንባር ሞክሮት የወጣበት ኳስ የቡድኑ የተሻለ ሙከራ ነበር። ከከነዓን መቀየር በኋላ ቡድኑ በአመዛኙ ፊቱን ወደ ተሻጋሪ ኳሶች ቢያዞርም ቡድኑ የፈጠራቸው ዕድሎች ሳማኬን የሚፈትኑ አልነበሩም።

58ኛው ደቂቃ ላይ ከሄኖክ አዱኛ ከተቀማ ኳስ በረከት አመቻችቶለት በሽመክት አማካይነት ወደ መሀል በመላክ አደገኛ ዕድል ፈጥረው የነበሩት ፋሲሎችም የተጋጣሚያቸውን ጫና መቋቋም ባይከብዳቸውም ተጨማሪ ዕድሎች መፍጠር ላይ ግን ተደክመው ታይተዋል። ጊዮርጊሶች የአቻነት ግብ ፍለጋ ፊት መስመር ላይ በቁጥር በርክተው በሚገኙባቸው አጋጣሚዎች ከኋላ የሚኖረውን ክፍተት መጠቀም ላይ አፄዎቹ እምብዛም ትኩረት አላደረጉም። 85ኛው ደቂቃ ላይ ማታሲ በአግባቡ ማራቅ የተሳነውን ኳስ በሱራፌል ተቀይሮ የገባው በዛብህ መለዮ ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት አጋጣሚም የቡድኑ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሆኖ አልፏል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአመዛኙ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉበት ፋሲሎችም ጨዋታውን አቀዝቅዘው ለመጨረስ የሞከሩበት እንቅስቃሴ በበዓምላክ ተሰማ ፊሽካ መቋጫውን ሲያገኝ ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ የዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥቦች በእጁ ማስገባት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ