” ከቂም ወጥተን እንደ ሀገር ብናስብ መልካም ነው ” – ዳዋ ሆቴሳ

የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል ወላይታ ድቻን በመርታት ማሳካት የቻሉት ሆሳዕናዎች ወሳኝ ሦስት ነጥቦች እንዲያገኙ ካስቻለው ዳዋ ሆቴሳ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ያለፉትን ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ ከተመለከትናቸው ምርጥ አጥቂዎች ተርታ የሚመደበው ዳዋ ከቀድሞ አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ ጋር ሀዲያ ሆሳዕናን መቀላቀሉ ይታወቃል። በነብሮቹ ማልያ በዛሬው ዕለት የመጀመርያውን ጨዋታ ያደረገው ዳዋ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ አሸንፎ እንዲወጣ ድንቅ ቅጣት ምት በማስቆጠር እና ዱላ ሙላቱ ላስቆጠረው ጎል ቀጥተኛ ምክንያት በመሆን ድርሻው ከፍተኛ ነበር። እጅግ ደምቆ ከዋለው እና የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን እያሳየ የሚገኘው ዳዋ በተለይ በብሔራዊ ቡድን ያለመመረጡ ምክንያት እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አግኝተነው ላቀረብንለት ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም። ትንሽ ቀዝቀዝ ብለን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ነው ሁላችን ተነሳስተን የተሻለ መንቀሳቀስ የቻልነው። አዲስ አበባ ቀድመን መጥተን ልምምድ አለመስራታችን አየሩ ከብዶናል። የተጫወትንበት ሰዓት በራሱ ከባድ ነበር። ያም ቢሆን ድክመቶቻችንን አስተካክለን ጥሩ መንቀሳቀስ በመቻላችን የምንፈልገውን ነጥብ አሳክተናል። የቅጣት ምት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ ነው እመታ፣ እለማመድም የነበረው። በግሌም በጣም ነው የምሰራው። ይህ ነገር ደግሞ በጣም ጠቅሞኛል። በቀጣይም ከቆመ ኳስ ብቻ ሳይሆን በእንቅስቃሴ ከኔ ጎል ማግባት ይጠበቃል። ዛሬ ጎል ማስቆጠሬ እና ጥሩ መንቀሳቀሴ ለቀጣይ ጨዋታዎች በራስ መተማመኔን እየጨመረው ይሄዳል። እንደ ቡድን ሀዲያን እያገለገልኩ በግሌ ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፋለው ብዬ አስባለው። በብሔራዊ ቡድን ጥሪን በተመለከተ የማስበው አሰልጣኞች ብሔራዊ ቡድንን ስይዙ ከቂመኝነት ነፃ መሆን ያስፈልጋል። በፊት የነበረህን ዕይታ ትተህ ሀገራዊ ነገር ማስቀደም አለብህ። ከዚህ የበለጠ እንቅስቃሴ ማድረግ አይጠበቅብኝም። ሜዳ ላይ ያለውን ነገር እያያችሁ ነው። ስለዚህ ከተለያዩ የማይጠቅሙ አስተሳሰቦች ወጥተን የተሻለው እና ጥሩ የተንቀሳቀሰው በብሔራዊ ቡድን ቢጫወት ጥሩ ነው። እኔ ማንም ተጫወተ ማንም ሀገራችን ውጤታማ ትሁን እኔ ባለመመረጤ ምንም አይመስለኝም። በቀጣይ ጠንክሬ እሰራለሁ።”

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀዲያ ሆሳዕናው ምክትል አሰልጣኝ እያሱ መርሐፅድቅ ስለ ዳዋ ሆቴሳ ይሄን ተናግረዋል።

“ስለዳዋ ምንም መናገር አይቻልም። ዳዋ እንደ ክለብ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም አሉን ከምንላቸው ተመራጭ አጥቂዎች አንዱ ነው። ግብ አካባቢም የተሻለ ተፅዕኖ አለው ቅጣት ምትም በማስቆጠር ይታወቃል። ያንን ነው ዛሬም ተግባራዊ ያደረገው። ልምምድ ላይ የሚያሳየውን ጨዋታ ላይም ደግሞታል። የዕለቱ ኮከብ ነው ማለት እንችላለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ