የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 2-0 ጅማ አባ ጅፋር

ከሱፐር ስፖርት ጋር የተደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኞች ድህረ ጨዋታ ቆይታ ይሄን ይመስል ነበር።

አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው…

“ጨዋታው ብዙም አላስደሰተኝም። ቡድኔ ከሦስቱ ጨዋታ አገግሞ ሦስት ነጥብ ማግኘቱ በራስ መተማመኑን ይጨምርለታል። በጨዋታው ግን ብዙም ደስተኛ አይደለሁም።”

መሻሻል ስላለባቸው ነገሮች…

“አሁንም ፊት ላይ ያለው ችግር እስካሁን አልተቀረፈም። ከዕረፍት በፊት የሳትናቸው ኳሶች ጫና ፈጥረውብናን። ሁለተኛ በሦስት ጨዋታ ቡድኑ ባላገኘው ውጤት ውስጣቸው ጥሩ ነገር ስለሌለ አንድ ጎል ለማስጠበቅ ሲሉ ማፈግፈግ አብዝተው ወደ መጠቃትም ሄደን ነበር። በሦስት ጨዋታ ገጥሞን የማያውቀው ነገር ነው የገጠመን። ገና ብዙ የምንሰራው ነገር አለ ፤ አስደሳች አይደለም። ሦስት ነጥቡ ግን ለነገ ስንቅ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው…

“እንዳያችሁት ነው ከዕለት ወደ ዕለት መሻሻሎች ነበሩ። በደንብ ኳሱን ተቆጣጥረን ተጫውተናል። ብዙ ኳሶች ስተናል ፤ ይህም የወዳጅነት ጨዋታዎች እጥረት ነው። ከዕረፍት በፊት ነበር መጨረስ የነበረብን። በአጋጣሚ ግን አልተሳካም። ብዙ የተከፋሁበት ነገር የለም ዘጠናውን ደቂቃ ኳስ ይዞ መጫወት ማለት በእዚህ ዓይነት አጭር የዝግጅት ጊዜ እና ካሉት አንዳንድ ንባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ብዙ አልተከፋሁም።”

ስለቀጣይ ጉዞ

“ብዙ ጨዋታዎች አሉ። ድጋፍ እስካለን ድረስ የሚደረገውን ነገር ለማድረግ እስከመጨረሻው ድረስ የጅማ አባ ጅፋር ደጋፊ እና ሕዝብ አደራ ስላለብኝ እታገላለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ