ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ ባህር ዳር ከተማን በቶማስ ስምረቱ ብቸኛ ግብ በመርታት ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

ወላይታ ድቻን አሸንፎ በነበረበት ጨዋታ ከተጠቀመበት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረገው ወልቂጤ ከተማ ሥዩም ተስፋዬ፣ አሚን ነስሩ እና አህመድ ሁሴንን በዳግም ንጉሤ ፣ በኃይሉ ተሻገር እና አብዱራህማን ሙባረክ ቦታ ተጠቅሟል። በአንፃሩ ባህር ዳር ከተማ ከአዳማው ጨዋታ ባደረገው ብቸኛ ለውጥ ጉዳት የገጠመው ሳምሶን ጥላሁንን በበረከት ጥጋቡ ተክቷል።

ባህር ዳር ከተማዎች ከወትሮው በተለየ ደክም ያለ የጨዋታ አጀማመር ባደረጉበት ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ወልቂጤዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለው ነበር። በ4ኛው ደቂቃ ያሬድ ታደሰ ከባህርዳር ሳጥን በቅርብ ርቀት ወልቂጤዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ ወደ ግብ ቢለሰክም ግቡን ቋሚ ለትማ በተመለሰችበት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል።

እየተቀዛቀዘ በመጣው የመጀመሪያ አጋማሽ
በ31ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን ወደ ግራ ካደላ አቅጣጫ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የባህርዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ በአግባቡ ኳስን መቆጣጠር ባለመቻሉ ያተገኘውን ቶማስ ስምረቱ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ባህር ዳር ከተማዎች በ24ኛው ደቂቃ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ካመከናት ነፃ የግንባር ኳስ በተጨማሪ በ42ኛው ደቂቃ ሰለሞን ወዴሳ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው ኳስ ግብ ለመሆን የቀረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባህር ዳር ከተማዎች ውጤቱን ለመቀልበስ በተጋጣሚ ሜዳ ቁጥራቸውን አብዝተው ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል። ይህም ሁኔታ ለወልቂጤ ከተማዎች መልሶ ማጥቃት ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈጥር ተስተውሏል።

ወልቂጤ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በተለይም በ66ኛው ደቂቃ በሀይሉ ተሻገር ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ የላከውና በመናፌ ዐወል ተጨርፋ አግዳሚ የመለሳት እንዲሁም ከአንድ ደቂቃ በኃላ አህመድ ሁሴን ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ ከሀሪስተን ሄሱ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ለማመን በሚከብድ መልኩ ያመከናት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ሲሆን ባህርዳር ከተማዎች በዚሁ አጋማሽ በባዬ ገዛኸኝ፣ ፍፁም ዓለሙና ምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የወልቂጤው አልሳሪ አልመህዲ ከጥቂት ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ቆይታ በኃላ በ 79ኛው ከፍቅረሚካኤል ዓለሙ ጋር የአየር ኳስ ማሸነፍ ሲታገል በክርን በማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች ጫና ለመፍጠር ሙከራዎች ያደረጉ ቢሆንም ባዬ ገዛኸኝ ከርቀት መትቶ ጀማል ካመከነበት ሙከራ ውጪ ጠንካራ ዕድል መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ክስተት ሳይታይበት በወልቂጤ ከተማዎች የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ