ሪፖርት | ጅማ እና ሀዋሳ በመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች አቻ ተለያይተዋል

በሁለቱም መረቦች ላይ የተቆጠሩት የምኞት ደበበ ጎሎች የጅማ እና የሀዋሳን ጨዋታ በ 1-1 ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርገዋል።

ጅማ አባ ጅፋር ከድሬዳዋው ጨዋታ አንፃር ጄይላን ከማል እና ተመስገን ደረሰን በአዳላሚን ናስር እና ሙሉቀን ታሪኩ ሲተካ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ቡናን ከረቱበት ጨዋታ የመስመር ኤፍሬም አሻሞን በብርሀኑ በቀለ የለወጡበትን ብቸኛ ቅያሪ አድርገዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ አብዛኛዎቹ ደቂቃዎች በጅማ አባ ጅፋር ሜዳ ላይ ነበር ያለቁት። ኳሱን ለሀዋሳዎች በመተው ጥንቃቄ ላይ ያተኮሩት ጅማዎች አልፎ አልፎ ብቻ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክሩ ይታይ ነበር። ቡድኑ የፊት አጥቂው ብዙአየሁ እንዳሻውን በ23ኛው ደቂቃ በጉዳት ካጣ በኋላም ይበልጥ አፈግፍጎ ታይቷል። 32ኛው ደቂቃ ላይ ንጋቱ ገብረስላሴ ከማዕዘን ምት የመጣን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ ብቻ ነበር የጅማ የተሻለ ሙከራ።

በአመዛኙ በቀኝ በኩል ባደላ ማጥቃት የኳስ ቁጥጥሩን ይዘው የተጫወቱት ሀዋሳዎችም በቅብብል የጅማን የመከላከል ግድግዳ ጥሰው መግባት ተስኗቸው ታይተዋል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ የጋብርኤል አህመድን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ይዞ በመግባት የሞከረው እና 33ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዘካርያስ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የመታው በጃኬ ፔንዜ ጥረት የዳኑ ኢላማቸውን የጠበቁ የቡድኑ ሙከራዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ ሀዋሳዎች ከተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጉትም ሙከራ ሳይሳካ ጨዋታው ተጋምሷል።

ሁለተኛው አጋማሽ የጅማ መከላከል ይበልጥ ጥብቅ ሆኖ የተመለሰበት ነበር። ከሳዲቅ ሴቾ በቀር የመስመር አጥቂዎቻቸውን ጭምር ወደ ኋላ የመለሱት ጅማዎች ተጋጣሚያቸው ምንም ቀዳዳ እንዳያገኝ ሰርተዋል። በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ይከሽፍባቸው የነበሩት ጅማዎች በመከላከሉ ግን ሙከራም ሳይደረግባቸው እስከመጨረሻው መዝለቅ ችለዋል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ኤልያስ አታሮ ከግራ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት የሀዋሳው ምኞት ደበበ ጨርፎ ጅማን ቀዳሚ ያደረገች ጎል በራሱ ላይ አስቆጥሯል። ክፍተት ፍለጋ አመዛኙን የጨዋታ ጊዜ በጅማ በር ላይ ያሳለፉት ሀዋሳዎች ባለቀ ሰዓት ተሸናፊ ከመሆን የታደጋቸውንም ጎል ይያገኙት ከምኞት ደበበ ሆኗል። ግዙፉ ተከላካይ በጭማሪ ደቂቃ ከዘነበ ከድር በተነሳ እና በኤፍሬም አሻሞ በተመቻቸለት ማዕዘን ምት መሬት ለመሬት የደረሰውን ኳስ በማስቆጠር ቡድኑን ከሽንፈት የታደገበትን ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በ 1-1 ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ