የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-1 ሀዋሳ ከተማ

ከዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ሁለቱ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

ኮምፓክት ሆነን ነው የተጫወትነው ፤ በመከላከሉ ላይ አዘንብለናል። ወደፊት የምንሄዳቸው ኳሶች ጥሩ ነበሩ። እንደቡድን ለመሆን ሞክረናል። ካለን የዝግጅት ጊዜ አንፃርም ልጆቼ ያላቸውን ፍላጎት ለእናንተ እተወዋለው። ግን ያው ኳስ ውበቱም ደስ የሚለው እዚህ ላይ ነው። እና በመጨረሻ ሰዓት ከራሳችን የጥንቃቄ ስህተት የተቆጠረችብን ጎል አለች። ብናሸንፍ ደስተኛ ነበርኩኝ ፤ ብዙም አልተከፋሁም ፣ ብዙም አልተደሰትኩም። ያለው ነገር ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ ወደፊት።

ስለተጫዋቾች ተነሳሽነት

ፊሽካ ከተነፋ ጀምሮ ያላቸው እልህ ከዚህ በፊትም እንደተመለከትነው ነው። እንደዚህ ዓይነት ቡድኖች በመስራት ነው የምታወቀውም ፤ ልጆቹ ፍላጎት እንዲኖራቸው ነው። አሁንም ብዙ ቀሪ ጨዋታዎች አሉ። ምንም አልተራራቅንም አንደኛው እኮ አስር ነው ፤ እኛ ሁለት ነን። ከሀያ በላይ ጨዋታዎች አሉ። ስለዚህ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል። ከተጋገዝን ከተባበርን ጥሩ ነገር መስራት ይቻላል። ወጣቶችም የተደባለቁበት ቡድን ነው። ከአሁን በኋላ ለሚኖረውም እንደእግዚያብሔር ፍቃድ ጥሩ ነገር ለመስራት እንታገላለን።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታው የፈራነውን ያህል ነበር። እንደዚህ እንደሚሆኑ እናውቅ ነበር። ግን ቢሆንም እኛ ከእነሱ ተሽለን 90 ደቂቃ ሙሉ ኳስ እንጫወት ነበር። ግን ወደ ጎል አስከፍቶ ለመሄድ አሁንም ችግሮች አሉብን። ለዛም እነሱ በአጋጣሚ በመጡበት ራሳችን ላይ ተጨርፎ ገብቷል። እንደዛም ሆኖ እኛም በአለቀ ሰዓት አግብተን 1-1 ሆነናል።

ለማስከፈት ስለተጠቀሙበት ቅያሪ

ተጨዋች ቅያሪ ያደረግነው እንሱ ከኃላ ብዙ ስለነበሩ ኳስ ቶሎ ወደ አጥቂዎች ለማድረስ የሚሻሙ ኳሶችን ነበር ለመጠቀም ያሰብነው ፤ ያም ሆኖ አልተሳካም። የገባው ኳስ ግን እንደዛው የማዕዘን ምት ኳስ ነበር ከመስመር ፤ በዛ መንገድ ነበር ያሰብነው እነሱ ግን ተሳክቶላቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ