ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከድል ጋር ታርቋል

ረፋድ ላይ በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በዳዊት ተፈራ ፍፁም ቅጣት ምት ወልቂጤን 1-0 አሸንፏል።

ሲዳማ ቡና ነጥብ ከተጋራበት ከአዳማው ጨዋታ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ጉዳት የገጠመው ይገዙ ቦጋለ ፣ ግርማ በቀለ ፣ አበባየሁ ዮሀንስ እና አማኑኤል እንዳለን በተመስገን በጅሮንድ ፣ ብርሀኑ አሻሞ ፣ ዮናታን ፍሰሀ እና ዳዊት ተፈራ ተክቷል። ወልቂጤዎች ደግሞ ከባህር ዳሩ ጨዋታ አሰላለፋቸው በተስፋዬ ነጋሽ እና አህመድ ሁሴን ምትክ በኃይሉ ተሻገር እና አብዱርሀማን ሙባረክን ተጠቅመዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የሲዳማ ቡናን የጨዋታ ፍላጎት በጉልህ ያሳየ ነበር። በአንፃሩ በወቅታዊ አቋም የተሻሉ የነበሩት ወልቂጤዎች ተቀዛቅዘው ታይተዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ሲዳማዎች አጥቂያቸውን በጉዳት አጥተዋል። በዚህም አዲሱ አቱላ በጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ምክንያት በአማኑኤል እንዳለ ተቀይሮ ወጥቷል። ያም ቢሆን ሲዳማዎች የተጋጣሚያቸውን ፈጣሪ ተጫዋቾች በመቆጣጠር የተሻለ ጊዜ ሲያሳልፉ ወደ ፊት በመሄዱ ግን እምብዛም ነበሩ።

3ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጊት ጋትኮች በረጅሙ አሻምቶት ተመስገን በጅሮንድ ከሳጥን ውስጥ የሞከረው እና የ17ኛው ደቂቃ የዳዊት ተፈራ የርቀት ሙከራዎች ብቻ ከሲዳማ በኩል የታዩ ደህና ሙከራዎች ነበሩ። ሆኖም 36ኛው ደቂቃ ላይ ከአማኑኤል እንዳለ የተነሳን ኳስ ቶማስ ስምረቱ በእጅ በመንካቱ ቡድኑ ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ ማስቆጠር ችሏል። በጭማሪ ደቂቃ በአብዱራሀማን ሙባረክ የቅጣት ምት ኳስ ብቻ መሳይ አያኖን የፈተሹት ወልቂጤዎች ግን የሲዳማ ሳጥን ውስጥ ዘልቀው መግባት ያልቻሉበትን አጋማሽ አሳልፈዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ወልቂጤዎች ፍጥነት ጨምረው ሲገቡ ሲዳማዎችም ማፈግፈግን ምርጫቸው አላደረጉም። 56ኛው ደቂቃ ላይ በያሬድ ታደሰ የግራ መስመር በከባድ መልሶ ማጥቃት ከፍተው ወደ ሙከራነት መቀየር ያልቻሉት ወልቂጤዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ በፍሬው ሰለሞን የረጅም ርቀት ሙከራ አድርገዋል። በታታሪነት የተጋጣሚያቸውን ፍጥነት እንዳይቀጥል እያደረጉ የመጡት ሲዳማዎችም በወልቂጤ ሜዳ ላይ በጥሩ አካሄድ ሳጥኑ አቅራቢያ በተደጋጋሚ ሲገኙ ቢታዩም የመጨረሻ ቅብብሎቻቸው ስኬት መውረድ አደገኛ የግብ ዕድል ከመፍጠር አግዷቸዋል።

አጥቂዎቻቸው አህመድ ሁሴን ፣ አሜ መሀመድ እና አቡበከር ሳኒን አከታትለው ያስገቡት ወልቂጤዎች የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥረዋል። ቀስ በቀስ ጨዋታውን ማቀዝቀዝ የቻሉት ሲዳማዎች ግን ጭማሪ ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ገዛኸኝ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው በጀማል ጣሰው ቢድንባቸውም የወልቂጤን ጫና አፍነው ጨዋታውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ