የዋልያዎቹ አሠልጣኝ መግለጫ ሰጥተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለስድስት ቀናት ያደረገውን የሁለተኛ ዙር የዝግጅት ምዕራፍ አስመልክቶ ዛሬ ከሰዓት መግለጫ ተሰጥቷል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጋቢት አጋማሽ ላለበት የምድቡ አምስተኛ እና ስድስተኛ ጨዋታ ዝግጅቱን በተለየ መርሐ ግብር እያከናወነ ቆይቷል። ከሳምንታት በፊት ጅማ ላይ የአንደኛ ምዕራፍ የዝግጅት ጊዜውን ለሦስት ቀናት ያደረገው ቡድኑም የሁለተኛ ምዕራፍ ዝግጅቱን ከየካቲት 1-6 አዲስ አበባ ላይ አከናውኗል። ይህንን የስድስት ቀን የዝግጅት ጊዜን አስመልክቶም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ወሎ ሠፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህንፃ መግለጫ ሰጥቷል።

ለአርባ ደቂቃዎች በቆየው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሠልጣኙ ጥሪ ስለተደረገላቸው ተጫዋቾችን፣ የተሰሩ የልምምድ መርሐ ግብሮችን፣ ጥሪ ቀርቦላቸው ስብስቡን ስላልተቀላቀሉ ተጫዋቾች፣ ስለቡድኑ ቀጣይ የዝግጅት ጊዜ እና ስለ ቀጣይ የቡድኑ ወሳኝ ጨዋታን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ስለ ዝግጅቱ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“የሁለተኛ ምዕራፍ የዝግጅት ጊዜያችን የማዳጋስካር እና ኮትዲቯር ጨዋታ ላይ ያተኮረ ነበር። 28 ተጫዋቾችን ጠርተን 24ቱን አግኝተናል። ለስድስት ቀናትም በቀን አንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምድ ሰርተናል። በቆይታችንም ታክቲካል የሜዳ ላይ ስራዎችን እና የክፍል ውስጥ የንድፈ ሀሳብ ትምህርቶችን ሰጥተናል። በዚህ የስድስት ቀን ዝግጅት ማድረግ ያልቻልነው ብቸኛ ነገር ጨዋታ ብቻ ነው። ሁሉም ክለቦች ዕረፍት ላይ ስለነበሩ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማድረግ አልቻልንም። እርስ በእርስም ለመጫወት አስበን ነበር ነገር ግን አልሆነልንም። በአጠቃላይ ልምምዱ ላይ ተጫዋቾቹ ያሳዩትም ነገር የሚደነቅ ነበር። በቀጣይ የሦስተኛ ምዕራፍ የልምምድ ጊዜያችንን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ (መጋቢት 3) ከውነን ለማዳጋስካሩ ጨዋታ እንቀርባለን። ከጨዋታውም በፊት ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ እናስባለን። እንደውም ጉዳዩ በፌዴሬሽኑ በኩል እየተሰራበት ነው።” ብለዋል።

አሠልጣኙ ከአምስት ደቂቃ ያልዘለለ ገለፃቸውን ካቀረቡ በኋላ በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን ሰንዝረውላቸው ምላሾችን መስጠት ጀምረዋል።ጥሪ ቀርቦላቸው ስብስቡን ስላልተቀላቀሉ ተጫዋቾች…?

“የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ጥሪ ስናቀርብ ጥሪው ያልተለመደ ነበር። በተጨማሪም ለክለቦች ጥያቄ የላክነው ዘግይተን ነበር። በጊዜውም ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘግይተን ለተጫዋቾቹ ጥሪ በመላካችን ምክንያት ተጫዋቾቹን መልቀቅ እንደማይችል በደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ገልጿል። ግን በተለያዩ አካላት እንደተነገረው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ አደለም ጥሪ ቀርቦላቸው ያልመጡት ተጫዋቾች። ከኢትዮጵያ ቡና ታፈሰ ሰለሞን እንዲሁም ከፋሲል ከነማ አምሳሉ ጥላሁን ሙሉ ለሙሉ ልምምዱን አልሰሩም። በተጨማሪም ያሬድ ባዬ የመጨረሻ ቀን የልምምድ መርሐ ግብሩ ላይ ብቻ ነው የተሳተፈው።

“ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድን ከምንም በላይ እንደሆነ ማወቅ እና መረዳት አለባቸው። ክለቦችም በተመሳሳይ ይህንን መገንዘብ አለባቸው። ለዚህኛው ዝግጅት ከ10 ቀን በፊት ነበር ለክለቦች እና ለሊግ ኮሚቴው ጥሪ የላክነው። ይህንን ተከትሎ ተጫዋቾች እንመጣለንም ሆነ አንመጣም ለማለት ጊዜ ነበራቸው። ሌላ ተጫዋች እንዳንጠራ እንኳን ወዲያው አንችልም አላሉንም። መቅረት አንድ ስህተት ሆኖ ሳይናገሩ መቅረት ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ስህተት ነው። ግን እኛ የተሳሳቱት ባለማወቅ ነው ብለን እናስባለን። ስለዚህ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ከመሄዳችን በፊት ማስተማሩ ይቀድማል ብዬ አስባለሁ። ተጫዋቾቹ ወጣትም ስለሆኑ በቅድሚያ እናስተምራቸው። ግን ሁላችንንም የሚገዛ ነገር እንዲኖር እንሞክራለን።ግን ሳልገልፅ ማለፍ የማልፈልገው ነገር በስብስቡ ውስጥ የነበሩት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ትክክለኛ ምሳሌ ናቸው። እንደ ጀማል፣ መስዑድ፣ ጌታነህ እና አስቻለው አይነቶቹ ትክክለኛ ልምድ ያላቸው ተምሳሌቶች ናቸው።”

ስለ ባህር ዳሩ ቀጣይ ዝግጅት…?

“በባህር ዳሩ ዝግጅት ያን ያህል ብዙ አዳዲስ ተጫዋቾችን የምንጠራ አይመስለኝም። የጉዳት እና ሌላ ነገር ከሌለ በስተቀር ያሉትን ለማስቀጠል እንሞክራለን። ግን የሚሆነው ነገር አይታወቅም። በተጠሩት እና ባልተጠሩት ተጫዋቾች መካከል ያለው ልዩነት ያን ያህል ሰፊ ስላልሆነ የሚኖሩ ክፍተቶችን ብቻ አይተን ውሳኔ እንወስናለን።”

ስለ ማዳጋስካሩ ጨዋታ…?

“በዋናነት ማዳጋስካሮች እኛ ጋር ሲመጡ አንድ ነጥብ አስበው ነው። ይህንን ተከትሎ ዝግጅታችንን እዚኛው ነገር ላይ በማድረግ ከውነናል። የግድ ይህኛውን የማዳጋስካር ጨዋታ ማሸነፍ አለብን።”

ስለ ውጤት…?

” እኔ ከባድ ሰዓት ነው ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀልኩት። እንደምታቁት ብዙ ነገሮች ቆመው ነበር። ይህንን ተከትሎ ስራዎችን መስራት ከባድ ነበር። እኔ ግን አሁን ላይ በዋነኝነት ሂደቱ ላይ ነው የምጨነቀው። እኛን የሚመስል ቡድን ለመገንባት እየሞከርን ነው። ውጤቱ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ አልፈልግም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ