ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና

ነገ ከሰዓት የሚደረገውን የሳምንቱ ሁለተኛ ጨዋታ በዚህ መልኩ ዳስሰናል።

ሲዳማ መሻሻል አሳይቶ አራት ነጥቦችን ካገኘባቸው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከተከታታይ ድሎች በኋላ አንድ ነጥብ ብቻ ካሳካባቸው የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች በኃላ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ቡና ሸርተት ያለበትን ፉክክር ልዩነት ላለማስፋት ሲዳማ ደግሞ በመሀሉ የሰንጠረዡ ክፍል ለመደላደል ውጤቱ ያስፈልጋቸዋል።

ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያቆመበት የመከላከል መንገድ አስገራሚ ነበር። ሁለቱን መስመሮች በመዝጋት እና የቡድኑን የፊት መስመር ተሰላፊዎች ሰው በሰው በመያዝ የተዋጣለት ዘጠና ደቂቃን አሳልፏል። በመልሶ ማጥቃቱ ረገድ ግን በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ነበር ወደ ፊት ሲሄድ የታየው። በነገው ጨዋታ ግን ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ኳስ ተቆጣጥረው ክፍተቶችን በመፈለግ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የሚገኙት ቡቡናዎች ጋር ላያዋጣ ይችላል። የኢትዮጵያ ቡና የቅብብሎች ብዛት እና የተጨዋቾች ቦታ መቀያየር ለዚህ የሲዳማ አቀራረብ ምላሽ ሊሆን ይችላል። በሌላ መልኩ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ዘልቆ መግባት የሚያዘወትሩት የቡናማዎቹ የመስመር ተከላካዮች እንቅስቃሴ የሲዳማ የመልሶ ማጥቃት ብቃት ዳግም እንዲታይ በር ሊከፍት ይችላል። ቡድኑ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ቀጥተኛ ኳሶችን ተመርኩዞ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጨዋታን አሸነፎ መውጣት የሚያስችል ብቃት እንዳለው የድሬዳዋው ጨዋታ ምስክር ይሆናል።

አሁንም በራሱ የግብ ክልል ላይ በሚፈጠሩ ስህተቶች ግቦችን በማስተናገዱ የቀጠለው ኢትዮጵያ ቡና ነገም መሰል ስህተቶችን ለማሰራት የተመቸ የአጥቂ ክፍል ይገጥመዋል። በተለይም ማማዱ ሲዲቤ እንደሰበታው ጨዋታ ሁሉ ስህተቶችን ፈጥኖ ወደ ግብ የመቀየር ብቃቱ ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድን ስጋት የሚሆን ነው። በማጥቃቱም ረገድ ቡድኑ በተጋጣሚ ጫና ውስጥ የሚገቡት የመሀል ተከላካዮቹ እና ፈንጠር ብለው የሚቆሙት የመስመር ተከላካዮቹ ኳስ ከኃላ መስርተው እንዲወጡ የሚያስችል ተለዋጭ ዕቅድ የግድ ያስፈልገዋል። በዚህ ላይ በተከላካይ አማካይ ሚና የሚጠቀማቸው ተጫዋቾች ላይ ተደጋጋሚ ለውጦች ሲያደርግ መታየቱ ከራስ ሜዳ የመውጣት ፈተናው ቀላል እንዳልሆነለት የሚጠቁም ነው። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ከግብ አስቆጣሪነት አለመራቁ እንደ ሀዋሳው ጨዋታ ክፍተቶችን ፈልጎ ወደ ውጤት መቀየሩ ላይ ላይቸገር እንደሚችል ያሳያል። ሚኪያስ መኮንን ባህር ዳር ላይ እንዳስቆጠረው ይዓይነት ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ተመተው የሚገቡ ጎሎችን ነገም ማግኘት የሚችል ከሆነም ተጨማሪ የግብ ማግኛ መንገድን ሊፈጥር ይችላል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና የጉዳት ዜና የሌለበት ሲሆን ሲዳማ ቡና አሁንም ጫላ ተሺታን እና ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የተጎዳው መሳይ አያኖን በጉዳት ካለመጠቀሙ ውጪ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ተቀይሮ የገባው አዲሱ አቱላን ጨምሮ ሌሎች ጉዳት ላይ የከረሙ ተጫዋቾቹ ወደ ልምምድ መጥተውለታል። ከዚህ ውጪ በአስረኛው ሳምንት ቀይ ካርድ የተመለከቱት ተክለማሪያም ሻንቆ እና ፈቱዲን ጀማል ከሁለቱም በኩል ጨዋታው ያልፋቸዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– እስካሁን በሊጉ ለ20 ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 8 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

– በ20 ግንኙነቶች 47 ጎሎች ሲቆጠሩ ሲዳማ ቡና 24 ፣ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 23 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኮች – ሰንዴይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ዮሴፍ ዮሐንስ – ብርሀኑ አሻሞ – ያስር ሙገርዋ

ተመስገን በጅሮንድ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ረመዳን ናስር – ዊሊያም ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ

© ሶከር ኢትዮጵያ