ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታ የበላይነት ጋር ሲዳማን በሰፊ ጎል ረትቷል

በዛሬው የከሰዓት በኋላ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 5-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የጅማ ቆይታውን አጠናቋል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከመጨረሻ ጨዋታቸው ሦስት ለውጦች አድርገዋል። ሲዳማ ቡና ቀይ ካርድ የተመዘዘበት ፈቱዲን ጀማልን በግርማ በቀለ ፣ ዳዊት ተፈራን በያስር ሙገርዋ እንዲሁም አዲሱ አቱላን በተመስገን በጅሮንድ ሲተካ ኢትዮጵያ ቡናም ቅጣት ላይ የሚገኘው ተክለማሪያም ሻንቆን በአቤል ማሞ ፣ ሬድዋን ናስርን በአማኑኤል ዮሃንስ እና አቤል ከበደን በሚኪያስ መኮንን ቦታ ለውጧል።

ጥሩ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ እንደተለመደው ኢትዮጵያ ቡና ኳስ ይዞ ሲንቀሳቀስ ሲዳማ ቡና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ጥረት አድርጓል። ቀዳሚውን አደገኛ አጋጣሚም 9ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች ሲያገኙ ማማዱ ሲዲቤ ከመሀል ሜዳው አለፍ ብሎ ባደረሰው ኳስ ጥሩ አጋጣሚ ቢያገኝም አዲሱ አቱላ ኳሱን ወደ ውጪ ልኮታል። ሲዳማዎች ሦስተኛውን የሜዳ ክፍል ለተጋጣሚያቸው ትተው በቆዩባቸው ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በ2ኛው እና 21ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ከደረሱባቸው አጋጣሚዎች ውጪ የግብ ዕሎችን ሳይፈጥሩ ቆይተዋል።

በቀጣይ ደቂቃዎች ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀዳሚ ሊሆኑ የሚችሉባቸው ዕድሎች መታየት ጀምረዋል። 24ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን በተከላካዮች መሀል ያሳለፈለትን ኳስ አቡበከር ናስር በፍቅሩ ወዴሳ አናት ላይ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። 31ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በቀኝ መስመር በኩል የገቡት ቡናዎች አቤል ከበደ ወደ ኃላ የመለሰውን ኳስ ዊልያም ሰለሞን ወደ ግብ ሞክሮ ፍቅሩ አድኖበታል። ይህን ተከትሎ የተሰጠውን የአስራት ቱንጆ የማዕዘን ምትም አበበ ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ዊልያም ሰለሞን 37ኛው ደቂቃ ላይ ከአቡበከር በተነሳ ኳስ ሌላ የሳጥን ውስጥ ዕድል አግኝቶም አሁንም ፍቅሩ ወዴሳ በድጋሚ አድኖበታል። በመከላከሉ ረገድ ክፍተት እየፈጠሩ የመጡት ሲዳማዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴያቸውም ስል ሆኖ ሳይታይ ቢቆዩም በመጨረሻ ሁለት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አድርገዋል። በዚህም በ39ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ በድንቅ ሁኔታ ካበረደው ኳስ መነሻነት ማማዱ ሲዲቤ በግራ መስመር ሳጥን ውስጥ በቀጥታ የመታው እና 43ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የሞከረው ኳስ በአቤል ማሞ ሊድኑ ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ ከግብ ክልላቸው ወጥተው ለመጫወት ሲሞክሩ 52ኛው ደቅቃ ላይ በፈጠሩት አጋጣሚ ዳዊት ተፈራ ያሾለከለትን ማማዱ ሲዲቤ በቀኝ በኩል ከጠባብ አንግል ላይ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ሆኖም ቡድኑ በቀደመ የመከላከል ትኩረቱ ላይ አለመገኘቱ በተከታታይ ግቦች እንዲያስተናግድ አድርጎታል። በዚህም አቤል ከበደ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ በግርማ በቀለ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት 59ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ማስቆጥሮ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም አቡበከር ከአስራት ቱንጆ በግራ መስመር የደረሰውን ኳስ በሁለቱ የመሀል ተከላካዮች መሀል ገብቶ ከመረብ ማገናኘት ችሏል። 68ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሚ ከአስራት ቱንጆ የተነሳው ኳስ በአቡበከር ተመቻችቶ ሀብታሙ ታደሰ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል።

ተደጋጋሚ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ሲዳማዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲጠብቁት የነበረው ስህተት ቢፈጠርም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ወንድሜነህ ደረጄ በግንባሩ ለአቤል ሊያደርስ ብሎ ያጠረውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ሙከራው ወደ ላይ ተነስቷል። ያም ቢሆን ቡናዎች ሲዳማን መቅጣታቸውን ቀጥለዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ 3 ለ 5 በሆነ የቁጥር ብልጫ ጎል አፋፍ ደርሰውም ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ባመቻቸው ኳስ አቡበከር ናስር የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ጎል አስቆጥሯል። የቡና የበላይነት ቀጥሎም ጭማሪ ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ አምስተኛ ጎል ከመረብ አገናኝቶ ቡና 5-0 ማሸነፍ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ ወጥቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ