“በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ጎል ማስቆጠር የተለየ ስሜት አለው” – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ፈጣኑ አጥቂ አማኑኤል ገብረሚካኤል በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ስላስቆጠረው የመጀመርያ ጎሉ ይናገራል።

የእርሱ ስኬት ጎልቶ መታየት የጀመረው መቐለ 70 እንደርታ በ2009 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ወሳኝ ሚና ሲጫወት እና የከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሲሆን ነው። ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ስኬታማ ሽግግር ማድረግ ያልተሳነው አማኑኤል የመቐለ ኮከብ ሆኖ መዝለቅ የቻለ ሲሆን በ2011 የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሱ የእሱ 18 ጎሎች እጅግ ወሳኝ ነበሩ። በተክለሰውነቱ ቀጠን ያለው አማኑኤል ፍጥነት እና ክህሎቱን በመጠቀም ከመስመር እየተነሳ አደጋ በመፍጠር እና በድንቅ አጨራረስ ጎሎችን በማስቆጠር ከሊጉ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ መሆን ችሏል።

አማኑኤል በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ምክንያት መቐለ በሊጉ የማይሳተፍ በመሆኑ በዘንድሮ ዓመት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለ ሲሆን ዘግይቶ ወደ ተሰላፊነት በመምጣት በቅርብ ጨዋታዎች ላይ መጫወት ጀምሯል። በዛሬው ዕለትም በአዲሱ ክለቡ የመጀመርያ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

አማኑኤል ዛሬ ጎል ስለማስቆጠሩ እና በቀጣይ ስለሚያስበው ነገር ተከታዩን አጭር ምላሽ ሰጥቶናል።

” የዘንድሮ ውድድሩ ለኔ ትንሽ ከበድ ይል ነበር። ምክንያቱም ከተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በኃላ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀልኩት። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከገባው በኃላ ከቡድኑ ጋር እስክዋሀድ ድረስ ትንሽ ተቸግሬ ነበር። በሒደት ግን ከጨዋታ ጨዋታ ወደ ትክክለኛው ቅርፅ በመግባት ከቡድኑ ጋር እየተላመድኩ በመምጣቴ ዛሬ ጎል ለማስቆጠር በቅቻለሁ። ከዚህም በኃላ የተሻለ ነገር ለመስራት እየሞከርኩ ነው።

” በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ጎል ማስቆጠር የተለየ ስሜት አለው። የመጀመርያ ጎሌን በማስቆጠሬ ደስ ብሎኛል። ስሜቱ ደግሞ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ጎሉን አግብቼ ደስታዬን ከገለፅኩበት መንገድ ይልቅ በውስጤ የገለፅኩት ደስታ ከፍተኛ ነበር።

” እስከ አስረኛው ሳምንት ድረስ ጎል አላስቆጠርኩም። እርግጥ ነው አጥቂ እንደመሆኔ መጠን ከኔ ጎል ይጠበቃል። ያው ቅድም እንዳልኩት ከቡድኑ ጋር እስክላመድ ድረስ ትንሽ ተቸግሬ ነበር። ይህም ቢሆን በእርግጠኝነት ወደ ጎል አግቢነቱ እንደምመጣ አውቅ ነበር። ለዚህም የቡድን አጋሮቼ ላፈረጉልኝ ድጋፍ አመሰግናለሁ። በተለይ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከጎል ብርቅም የብሔራዊ ቡድን ጥሪ እያደረገልኝ በራስ መተማመኔን ከፍ እንዲል አድርጎልኛል። በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን አመሰግናለሁ።

“ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ነው ጎል ማስቆጠርም ጀምሬአለው። ከዚህ በኃላ ጠንክሬ በመስራት እንደከዚህ ቀደሙ እራሴን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ ለማስገባት እንደምችል ተስፋ አድርጋለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ