ሪፖርት | ሀዋሳ እና ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

ሁለት ግቦች የተስተናገዱበት የአራት ሰዓቱ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በሰበታ ከተማ 2-1 ተረተው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት ሀዋሳዎች ከባለፈው አሰላለፍ ዘነበ ከድር እና ዮሐንስ ሰጌቦን በዳንኤል ደርቤ እና ወንድማገኝ ኃይሉ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ድሬዳዋን ገጥመው አቻ የተለያዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ የአብስራ ተስፋዬ፣ ሮቢን ንጋላንዴ እና አቤል እንዳለን አሳርፈው ከነዓን ማርክነህን፣ ሐይደር ሸረፋ እና ጋዲሳ መብራቴን ወደ ቋሚነት በማምጣት ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታውን በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት ፈረሰኞቹ ገና በጅማሮ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በሦስተኛው ደቂቃም ጋዲሳ መብራቴ መስፍን ታፈሰን የቀማውን ኳስ ለጌታነህ ከበደ አቀብሎት የቡድኑ አምበል ኳሱን ሜንሳ ሶሆሆ መረብ ላይ አሳርፎታል። ቡድኑ ግቡን ካስቆጠረ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም በቀኝ መስመር አጥቂ ቦታ ላይ ተሰልፎ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ተጨማሪ ጎል ለማስቀጠር ጥሮ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የነበረውን የጊዮርጊስ ጥቃት በሚገባ መመከት ያልቻሉት ሀዋሳዎች በ11ኛው ደቂቃ አቻ የሚሆኑበትን የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ (በእነርሱ በኩል) ሰንዝረዋል። በዚህ ደቂቃም ብሩክ ከመስፍን ጋር በጥሩ መናበብ ተቀባብለው ያገኘውን የመጨረሻ ኳስ ከሳጥን ውጪ መትቶት ባህሩ አምክኖበታል።

በ12ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅንጅት ሀዋሳ የግብ ክልል በድጋሜ የደረሱት ጊዮርጊሶች ጋዲሳ ከሀይደር ተቀብሎ ባመከነው ኳስ ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ሀዋሳዎችም ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን የመስመር ላይ ጥቃቶች ለመሰንዘር ሲጥሩ ታይቷል። በተጨማሪም ከቆመ ኳስ የሚገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክረዋል። በዚህ እንቅስቃሴም በ28 እና 30ኛው ደቂቃ አለልኝ እና ብሩክ በግንባራቸው ወደ ባህሩ በላኩት ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ከደቂቃ ደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት ሀይቆቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ኤፍሬም አሻሞ በሞከረው ጥሩ ኳስ ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። በድጋሜም በጭማሪው ደቂቃ ደስታ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ ነበር። ነገርግን ውጥናቸው ሳይሰምር አጋማሹ በፈረሰኞቹ መሪነት ተገባዷል።

እየተመሩ የመጀመሪያውን አጋማሽ ያጠናቀቁት ሀዋሳዎች ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ በወንድማገኝ ኃይሉ አማካኝነት ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ወዲያው ያመሩት ጊዮርጊሶች ደግሞ ከደቂቃ በኋላ አስቆጪ ዕድል አምልጧቸዋል። በዚህም ከነዓን ጋዲሳ ያቀበለውን ኳስ በግራ እግሩ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ያስመለከተው የሁለተኛው አጋማሽ በ53ኛው ደቂቃ ሀዋሳን አቻ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር። በዚህ ደቂቃ ወንድማገኝ ከኤፍሬም የተቀበከውን ኳስ ወደ ጎል ቢመታውም ኳሷ የግቡን ቀሚ ነክታ መዳረሻዋን ውጪ አድርጋለች።

ጨዋታው ቀጥሎም በ60ኛው ደቂቃ ይህኛውን አጋማሽ በተሻለ ተነሳሽነት የጀመሩትን ሀዋሳ ከተማዎች አቻ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃም ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ በቁጥር ብልጫን አግኝተው የጊዮርጊሶች የግብ ክልል ላይ የነበሩት ሀዋሳዎች እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ ያገኙትን ኳስ ሳያባክኑ በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረውታል። ጊዮርጊሶችም ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ ለመስጠት በማሰብ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ደርሰው በሄኖክ አማካኝነት የሞከሩት ሙከራ የግቡ ብረት መልሶባቸዋል።

ተከታታይ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ በእጃቸው የነበረውን መሪነት ዳግም ለማግኘት መጣር የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ74ኛው ደቂቃ ሙሉዓለም መስፍን ከቀኝ መስመር ተሻምቶ በግንባሩ ወደ ሜንሳ መረብ በላከው ኳስ ጥቃት ሰንዝረዋል። በተጨማሪም በ83ኛው ደቂቃም ግልፅ የግብ ዕድል ያገኘው ቡድኑ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው አቤል እንዳለ አማካኝነት ዕድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። ሀዋሳዎችም በመጨረሻ ደቂቃዎች ብልጫ ቢወሰድባቸውም ግባቸውን ለሁለተኛ ጊዜ ሳያስደፍሩ ወተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናገድ 1-1 ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ነጥባቸውን 17 ያደረሱት ሀዋሳዎች ባሉበት ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ሲቀመጡ ለ57 ያክል ደቂቃዎች የጨዋታው መሪ የነበሩት ጊዮርጊሶች ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህርዳርን በግብ ልዩነት በልጠው (በ26 ነጥቦች) ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ