ሪፖርት | ነብሮቹ ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን ድል ሲዳማ ላይ አግኝተዋል

የአስራ ስድስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የሀዲያ እና ሲዳማ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና 2ለ0 አሸናፊነት ተገባዷል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በባህር ዳር ከተረቱበት የመጀመርያ 11 ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል። በዚህም አይዛክ ኢሴንዴ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ተስፋዬ አለባቸውን በፀጋሰው ደማሙ ፣ አማኑኤል ጎበና እና ዑመድ ኡኩሪ ለውጠዋል። በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር አራፊ የነበሩት ሲዳማዎች ከመምራት ተነስተው ከተረቱበት የመጨረሻው የባህር ዳር ጨዋታ ስድስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም መሳይ አያኖ፣ ሰንደይ ሙቱኩ፣ ጊት ጋትኮች፣ ተመስገን በጅሮንድ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለን በፍቅሩ ወዴሳ፣ ግርማ በቀለ፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ያሬድ ከበደ እና ኦኪኪ አፎላቢ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

መመጣጠን የታየበት የመጀሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሀዲያ ሆሳናዎችን መሪ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር። በዚህም በ8ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ጥሩ ኳስ ለአዲስ ፈራሚው ዑመድ ኡኩሪ አመቻችቶለት ዑመድ ዕድሉን አምክኖታል። ከደቂቃ ደቂቃ የኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸው እያደገ የመጣው ሲዳማዎች ደግሞ በ13ኛው ደቂቃ በኦኪኪ አፎላቢ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል መፈተሽ ጀምረዋል። ይህንን ሙከራ ካደረጉ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ በላከው ሌላ ኳስ መሪ ለመሆን ጥረዋል።

ረጃጅም ኳሶችን ከፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጋር በማዳቀል ጨዋታውን የቀጠሉት ሀዲያዎች በ25ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሱሌይማን አሻምቶት መሀሪ በአግባቡ ማውጣት ያልቻለውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ቢስማክ አፒያ አግኝቶት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ከቆመ ኳስ ግብ አስተናግደው መመራት የጀመሩት ሲዳማዎች በጨዋታው በቶሎ ለመመለስ የሚያስችላቸውን ጎል ለማግኘት እጅግ ከብዷቸው ታይቷል። የሀዲያን የተከላካይ መስመር ሰብሮ መግባት ተስኗቸውም አጋማሹ ተገባዷል።

የሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ ተነሳሽት የጀመሩት ሲዳማዎች ያሬድ እና ኦኪኪን ዒላማ ያደረጉ የመስመር ላይ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም መሪ ለመሆን ሲታትሩ ተስተውሏል። ነገርግን ከኳስ ጀርባ በመሆን አጋማሹን የጀመሩት ሀዲያዎች በ55ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አስፍተው የሲዳማዎችን ልፋት ከባድ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃም የቡድኑ አምበል ዳዋ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ በሚገባ መቆጣጠር ያልቸለው የግብ ዘቡ ፍቅሩ ወዴሳ ሳያርቅ የተፋውን ኳስ መድሃኔ ብርሃኔ አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮታል።

በክፍት ጨዋታ ጠጣሩን የሀዲያ የተከላካይ መስመር ማስከፈት ያልቻሉት ሲዳማዎች በ70ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለቡድኑ እያደረገ በነበረው ኦኪኪ አፎላቢ የቅጣት ምት ጥቃት ሰንዝረዋል። ይሄው ቅጣት ምት ተጨርፎ በመውጣቱ ምክንያት የተገኘን የመዓዘን ምትም በድጋሜ ኦኪኪ ለማስቆጠር ጥሮ መክኖበታል። ሀዲያዎች በበኩላቸው ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥረውት የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች አሳልፈዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በሀዲያ ሆሳዕና አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ በዛሬው ጨዋታ ድል ያገኑት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ነጥባቸውን 26 በማድረስ አንድ ጨዋታ ከሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ አራተኛ ደረጃን ተረክበዋል። በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ሲዳማዎች ደግሞ በ14 ጨዋታ በሰበሰቡት የነጥብ ብዛት እኩል አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።




© ሶከር ኢትዮጵያ