​የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 2-0 ሲዳማ ቡና

ከዛሬው ረፋድ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው

ለእኛ ማሸነፍ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነበር። ለማሸነፍ የተደረገ ትግል ነው። ውጤቱንም በፀጋ ተቀብለናል።

ወደ ዋንጫው ፉክክር ስለመመለስ 

ሀዲያ በተከታታይ ሁለት ጨዋታ መሸነፉ ከለመደው ባህል ውጪ ነው። በተለይ ተከላካይ መስመራችን ላይ ወሳኝ የምንላቸው ተጫዋቾች አለመኖራቸው እና ቡድናችን ተሟልቶ ያለመግባቱ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። ሆኖም ግን አሁን የዑመድ መምጣት በቡድናችን ላይ የፈጠረው መነሳሳት አለ። ከጨዋታ የራቀ ተጫዋች ነው። ግን በሂደት ቡድኑ ላይ ሰርተን  የተሻለ ውጤት አምጥተን ሜዳሊያ ውስጥ ሆነን ለመጨረስ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። 

የቢስማርክ እና መድሀኔ ወደ ግብ ማስቆጠር መምጣት

ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ዛሬ ለማሸነፍ ወስነን ስናጠቃ በአራት ሰው ለመሄድ ነው የሞከርነው። መድሀኔ እና አፒያ ከፊት ደግሞ ሁለቱ አጥቂዎች አሉ። በዛ መልክ ነበር ያሰብነው እንደፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ ተሳክቶልናል። 

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

የተሻለ ተጫውተውም ስለመሸነፋቸው
                                                                             ያው አንዳንዴ የእግርኳሱ ተፈጥሮ እንደዛ ነው። በሥነ-ልቦና የበላይነት ሲወሰድብህ ትንሽ ስህተቶች ትፈጥራለህ። በስህተቶች ነው ሁል ጊዜ። እግርኳስ በራሱ ስህተቶችን ተጠቅመህ ማሸነፍ ነው። ግን የእኛ ደግሞ ሊሸፈኑ የማይችሉ ስህተቶች ናቸው። ይሄ የሥነ-ልቦና ጫና የፈጠረው ነው። በተለይ የዛሬን ጨምሮ ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች የሥነ-ልቦና የበላይነት ያላቸው ቡድኖች ናቸው የገጠምነው። ከዛ አንፃር መሸነፋችን ግድ ሆኗል ማለት ነው። ትንሽ የመሻሻል ሁኔታ ይታያል። ግን አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነው።

ቡድኑን ለመገንባት ጊዜ ስለማስፈለጉ

ያስፈልጋል አዎ ! ትንሽ ጊዜ አገኘን ቢባል ያሁኑ ስምንት ቀናት ናቸው። ከዛ በፊት በየአራት ቀኑ ጨዋታ ነው። ምንም ዓይነት ዝግጅት አላደረግንም። ተጫዋቾቹን ለማወቅ በጣም ከባድ ነው። አሁን ግን ሁሉንም ተጫዋቾች አውቄያለሁ ማለት ይቻላል። ከዚህ ቀጥሎ ያለው የዕረፍት ጊዜ ትንሽ ይረዳናል ብለን እናስባለን። እንግዲህ አሻሽለን ከዚህ ከአደጋው ለማምለጥ ጥረት እናደርጋለን። 

በሊጉ ለመቆየት ስለመቻላቸው

አዎ ፤ በአንድ ጨዋታ አንድ ደረጃ ፣ ሁለት ደረጃ ፣ ሦስት ደረጃ  የምናሻሽልበት ሁኔታ ነው ያለው። ሦስት ነጥብ እና ስድስት ነጥብ የት እንደሚያደርስህ ግልፅ ነው። ስለዚህ ከዚህ አንፃር መድረስ እንችላለን። በተለይ በተለይ ይሄን የሥነ-ልቦና ችግራችንን ከቀረፍን ማለት ነው።

ስለባህር ዳር ቆይታቸው

ከውጤት አንፃር ምንም የሚደበቅ ነገር የለውም ጥሩ አልነበረም። ግን በአጠቃላይ ባህር ዳር በቆየንባቸው ጊዜያቶች በጣም ጥሩ ጊዜ ነበረን። ሕብረተሰቡ ጥሩ ነው ፤ እዚህ አካባቢ ያለው ሁሉም ነገር ደስ ይላል። ከውጤት አንፃር ያጣነውን ነገር ደግሞ ድሬዳዋ ላይ እንሞክራለን። 


© ሶከር ኢትዮጵያ