​ቅድመ ዳሳሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ16ኛው ሳምንት መገባደጃ ቀን ማለዳ የሚደረገውን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

የዚህ ጨዋታ ነጥቦች አስፈላጊነት ከውጤት ለራቁት ተጋጣሚዎች ቀጣይ እጣ ፈንታ ወሳኝ ይሆናሉ። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ፈረሰኞቹ በሂደት ለሰንጠረዡ አጋማሽ መቃረባቸው ውድድሩን ሲጀምሩ ከነበራቸው ሀሳብ ጋር እጅግ የተራራቀ እንደመሆኑ በቶሎ ወደ ላይኛው ፉክክር መመለስን ይሻሉ። ሀዋሳ ከተማም ከድል ከተራራቀ ስድስት ጨዋታዎች አልፈውት እንደቀልድ ወደ አደጋ ዞኑ በመንሸራተት ላይ ይገኛል። በቢቢነገው ጨዋታ ከሳምንታት በፊት የነበረበትን ድንቅ አቋም መልሶ ካላገኘም ባህር ዳርን በመሳቀቅ ሊለይ ይችላል።

ሀዋሳ ከተማ ውጤት አጥቶ ከቆየባቸው ስድስት ጨዋታዎች በሦስቱ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። ያም ቢሆን የኋላ መስመሩ ላይ አልፎ አልፎ የሚታይበት የትኩረት ማነስ ግብ እንዲያስተናግድ መንስኤ እየሆነ ነው። በነገው ጨዋታም እንደ ጌታነህ ከበደ ካለ ልምድ ያለው አጥቂ ጋር እንደመገናኘቱ የተሻለ ወጥነት የሚንፀባረቅበት ላውረንስ ላርቴን ጥሩ ሆኖ መገኘት ይሻል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የሚታይበት የጨዋታ መጀመሪያ ተነሳሽነት መቀነስ በነገው ጨዋታ የሚያሰጋው ሌላ ጉዳይ ነው። እንደ ፋሲል እና ሰበታ ጨዋታ ግብ ከተቆጠረበት በኋላ የሚታይበት ጫና ፈጥሮ የመጫወት ሂደት ብቻውን ውጤት ለማምጣት የሚረዳ ባለመሆኑ ቀድሞ ጨዋታውን መቆጣጠር እና ግብ ማስቆጠር ጋር መታረቅ አስፈላጊው ነው።

ግቦችን ለማግኘት የመስመር ጥቃትን የመጀመሪያ ምርጫው የሚያደርገው ሀዋሳ ከተማ ነገ ከመጀመሪያው ዙር መርሐ-ግብር በተሻለ ጨዋታውን በጥንቃቄ እንደሚቀርብ ሲታሰብ ወደ ፊት ለመሄድ ግን አሁንም አማራጮቹ ሁለቱ መስመሮች ይመስላሉ። በቅርብ ጨዋታዎች ተለዋዋጭ አደራደሮችን ጥቅም ላይ ሲያውል የሚታየው ሀዋሳ በሁሉም ቅርፆች ውስጥ ከራሱ ሜዳ ከወጣ በኋላ የኳስ ስርጭቱ በሜዳው ስፋት ተመርኩዞ ወደ ግብ መድረሱ ከተጋጣሚው ጋር የሚያመሳስለው መሆኑ የጨዋታውን ዋነኛ ፍልሚያዎችም በዚሁ ቦታ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። በዚህ መንገድ ስኬታማ ለመሆን ግን ጥሩ ስኬት ያለው የማጥቃት ሽግግር ካልታከለበት በአጨራረስ ረገድ መዳከም እየታየባቸው የሚታዩት አጥቂዎች ከኳስ ጋር የተሻለ ጊዜ የሚያገኙበትን ቅፅበት ሊያሳጥርባቸው ይችላል።

ከሳምንታት በፊት በሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል እና ድሬዳዋ ጋር የግብ መንገዱ ጠፍቶት ከሜዳ ወጥቷል። የተሻለ ጥንቃቄን በተላበሱት በእነዚህ ተጋጣሚዎች ላይ አለማስቆጠሩም የማጥቃት ኃይሉ ከደካማ ተጋጣሚዎች ውጪ ያለውን ጥንካሬ እንዲመዝን የሚያደርገው ነው። በአሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ ፍጥነት እንዳነሰው የተነገረለት የቡድኑ የኳስ ምስረታ ሂደት ለዚህ አንዱ ምክንያት ሲሆን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ሳይሸጋገር የሚቀማቸው ኳሶችም ቡድኑን ለፈጣን ጥቃት ሲያጋልጡት ይታያል። በተለየም የግራ ወገኑ የመከላከል ክፍል በተደጋጋሚ ሲከፈት መታየቱ ከሀዋሳ የመስመር ጥቃት ምርጫ አንፃር ሊያሳስበው የሚገባ ነጥብ ነው።

የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያሉትን አማካዮች ቢቀያይርም ሁነኛ መፍትሄ ያላገኘው ጊዮርጊስ የተሻለ አስፈሪነትን ተላብሶ የሚታየው በአማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ውስጥ እየጠበበ የሚመጣ ጥቃት እና ከሄኖክ አዱኛ ተሻጋሪ ኳሶች ሆኖ ይታያል። ከእነዚህ ቦታዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠርም ነገ ከሀዋሳ የመስመር ተሰላፊዎች ጋር ከፍ ያለ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ከወቅታዊ አቋም አንፃር ግን ጊዮርጊስ በፈጣን ጥቃት ክፍት ሆኖ በታየባቸው ቅፅበቶች እየታደገው ያለው ባህሩ ነጋሽ ነገም ክለቡ ስለምን ወደ ውጪ እንደሚያማትር የሚያስጠይቅ ብቃት ማሳየት ይጠበቅበታል። 

በነገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጉዳት ያልነበረው አቤል ያለው እና በግል  ጉዳይ ከጨዋታ ርቆ የቆየው ፍሪምፖንግ ሜንሱን አገልግሎት እንደሚያገኝ ሲጠበቅ ቀሪው ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። በሀዋሳ ከተማ በኩልም ወንድምአገኝ ማዕረግ ብቻ በጉዳት ሳቢያ በጨዋታው የማይካተት ሲሆን ኤፍሬም ዘካርያስ እያገገመ እንደሚገኝ ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 41 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 25 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 71 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 32 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ– ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሐንስ

ወንድምአገኝ ኃይሉ – ዳዊት ታደሰ – አለልኝ አዘነ

ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ብሩክ በየነ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ባህሩ ነጋሽ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – አብዱልከሪም መሀመድ

የአብስራ ተስፋዬ – ናትናኤል ዘለቀ

አቤል ያለው – አቤል እንዳለ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ጌታነህ ከበደ

© ሶከር ኢትዮጵያ